የምርት እና የኢንዱስትሪ ማዕከሏ ቡሬ

0
179

ባሕር ዳር: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቡሬ ከተማ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከባሕር ዳር በደቡባዊ አቅጣጫ 148 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በ1540ዎቹ አጋማሽ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ቡሬ ከተማ በቡሬ ዙሪያ እና በጃቢ ጠህናን ወረዳዎች እንዲሁም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትዋሰናለች፡፡

ከከተማ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በተገኘ መረጃ መሠረት በውስጧ እና በዙሪያዋ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ቡሬን ልዩ ያደርጋታል፡፡ ለአብነትም ድሮ አምቦ ውኃ (አሁን ኩል ውኃ) እየተባለ የሚጠራው ተጠቃሹ ነው፡፡ ለዚህም፡-“ኧረ ቡሬ ቡሬ ቡሬ ከተማው ጠላ እንኳ ቢጠፋ ይጠጣል አንቦው” ተብሎ ይዘፈንላታል፡፡

የበርበሬ፣ የበቆሎ እና የጤፍ ምርቶችም ለቡሬ እና አካባቢዋ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ቡሬ ለኢንዱትሪ ፓርክ የተመቸች በመኾኗ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች ባለቤትም ናት፡፡ ቀደምቱን የኩል ውኃ ጨምሮ ከ12 በላይ የተለያዩ ፋብሪካዎች መነኻሪያ ናት፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ እንደ ሆቴል እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎችም ሞልተውባታል፡፡

ካሏት የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ መስህቦች ውስጥ ሃይማኖታዊ መስህቦች እና አገልግሎቶቿ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዲስ አበባ፣ ከወለጋ፣ ከባሕር ዳር እና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ አቅጣጫ የሚያገናኟት የአስፓልት መንገዶች እና በሌሎች መጋቢ መንገዶቿ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለግብዓት አቅርቦትም ኾነ ለምርት ስርጭት ምቹ ናት፡፡

መሠረተ ልማት የተሟላለት የቡሬ ኢንዱስትሪ መንደር ሌላው የቡሬ ሰው ሠራሽ ፀጋዋ ከኾነ ውሎ አድሯል፡፡ የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የሞባይል ኔትወርክ፣ የከተማ ውስጥ መሠረተ ልማት እየተስፋፋባት ያለች ከተማ ናት፡፡ ሠርቶ አደር፣ አምራች እና የመሸመት አቅም ያለው የቡሬ እና አካባቢው ሕዝብ በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ቢሠሩ አስተማማኝ ገበያ ኾኖ ያገለግላል፡፡

ቡሬ በዙሪያዋ የጤፍ፣ የበቆሎ እና የበርበሬ ምርት ከሚታፈስበት ጎጃም ምድር እንብርት ላይ ትገኛለች፡፡ በተፈጥሮም ኾነ በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ስትራቴጅካዊ ቦታ ናት፡፡ የአየር ንብረቷ ምቹነት ተጨምሮበት ቢያለሙባት የምታተርፍ፣ የእረፍት ጊዜን ቢያሳልፉባት አዕምሮን የምታድስ ምድርም ናት፡፡

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here