ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም!

0
209

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ኢትዮጵያዊ ትውፊቱን ያልለቀቀ እና ጥብቅ ሥርዓትን የተከተለ ሕይዎት የሚኖርበት ሃይማኖታዊ ቦታም ነው፡፡ ገዳሙ ከጎንደር ከተማ 132 ኪሎ ሜትር፣ ከመተማ ወረዳ ገንዳ ውኃ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ከደረቅ ዓባይ ቀበሌ በስተደቡብ የ3 ሰዓት የእግር ጉዞ ካደረጉ በኋላም ይገኛል፡፡

የማኅበረ ስላሴ አንድነት ገዳም በአራተኛው መቶ ከፍለ ዘመን በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ዘመን እንደተመሠረተ ይነገራል። የአሁኑን ስያሜ ከማግኘቱ በፊት “ምቋመ ሥላሴ”ይባል ነበር፡፡ የሺዎች ማኅበር እየተባለም ይጠራል፡፡ ማኅበረ ሥላሴ የሚለው ስያሜ በአጼ ፋሲለደስ እንደተሰየመም ነው የሚነገረው።

ማኅበረ ስላሴ አንድነት ገዳም ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ከነበሩ ነገሥታት ጋር የተሳሰረ ታሪክ እንዳለውም ይነገራል። ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ፣ ከአጼ አምደ ጽዮን፣ ከአጼ ልብነ ድንግል፣ ከአጼ ሱስንዮስ እና ከአጼ ፋሲለደስ ጋርም የተያያዘ ሰፊ ታሪክ አለው፡፡

ከሱዳን ድንበር አካባቢ በመገኘቱ ምክንያት በተለያየ ጊዜ ጥቃት ሲደርስበትም ቆይቷል፡፡ ከዮዲት እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በተደረጉ ጦርነቶች የገዳሙ በርካታ ቅርሶች ወድመዋል፡፡ ገዳሙ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎችንም ይዟል። የዲዛ፣ የእጣን ዛፍ፣ ሽመል፣ ዞቢ እና ቋራ የመሳሰሉት እፅዋት ዝርያዎች መገኛም ነው። እንደ ዝንጀሮ፣ ነብር፣ አጋዘን፣ ሜዳቋ የመሳሰሉ የዱር እንስሳት፣ እፅዋት፣ እዕዋፋት እና ተሳቢዎች ይኖሩበታል፡፡ ገንዳ ውኃ እና ሽንፋ በተባሉ ታላላቅ ወንዞች የተከበበም ነው። ገዳሙ የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ከመጠበቅ አኳያ ባለው ፋይዳ ተመሥርቶ በጥብቅ ሥፍራነት እንዲከለል ተደርጓል፡፡

በመረጃ ምንጭነት የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያሳተመው አማራ ድንቅ ምድር መጽሐፍን እና ኃይለ ማርያም ኤፍሬም ያሳተሙት የኢትዮጵያ ታሪክ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ የተሰኘ መጽሐፍን ተጠቅመናል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here