ፍኖተ ሰላም: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ1933 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የፍኖተ ሰላም ከተማ ከባሕርዳር 180 ኪሎ ሜትር፤ ከአዲስ አበባ 376 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
የቀድሞዋ ወጀት የአሁኗ የፍኖተ ሰላም ከተማ አመሠራረት ከንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ግንኙነት አለው።
ወቅቱ ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አምስት ዓመት ወረራ ነፃ የወጣችበት እና ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ሀገር ተነስተው በሱዳን ከዛም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል አድርገው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ፍኖተ ሰላም ከተማ ያርፋሉ።
በወቅቱ ቦታው ከሌሎች አካባቢዎች የተለየ ሰላም የሰፈነባት እና ለኑሮ ምቹ እንደኾነች በማየታቸው የወቅቱ ጠቅላይ ግዛት መቀመጫ ወጀት እንድትኾን አዝዘዋል።
በዚያን ጊዜ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በፊት ትጠራበት ከነበረው ”ወጀት” ወደ ”ፍኖተ ሰላም” እንዲቀየር አድርገዋል። ቃሉ የግዕዝ ቃል ሲኾን ትርጉሙም የሰላም መንገድ ማለት ነው።
ፍኖተ ሰላም ከተማ በወቅቱ ለቀድሞው ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በመኾን ያገለገለች ሲኾን በ1996 ዓ.ም ወደ ከተማ አሥተዳደርነት አድጋለች።
በ2004 ዓ.ም የምዕራብ ጎጃም ዞን መቀመጫ ለመኾን በቅታለች።
ፍኖተ ሰላም ከተማ ሁለት ትላልቅ ወንዞች የሚያልፉባት ከተማ በመኾኗ ለከተማ ግብርና ምቹ አድርጓታል።
በከተማዋ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የቱሪስት መስህብ የኾነ የተፈጥሮ ዋሻም ይገኛል።
ፍኖተ ሰላም ከተማ የገወቻ የተፈጥሮ ደን፣ የገራይ ግድብ፣ የቀረር ቁስቋም ገዳም፣ የገወቻ ዋሻዎች (ቁም ዋሻ እና ጅብ ዋሻ) ለቱሪስት መስብህነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቦታዎች መገኛ ከተማም ናት።
ከተማዋ በተለይ ሊለሙ የሚችሉ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ሀብቶች ያላት በመኾኗ ለኢንቨስትመንት ምቹነት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ናት።
ፍኖተ ሰላም ከተማ ባከል በሚባለው ቦታ በጣዕሙ ልዩ የኾነ የቡና ምርት መገኛም ጭምር ናት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!