ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 97/2004 ዓ.ም እውቅና አግኝቶ የተመሠረተ ነው፡፡ ጥብቅ ሥፍራው በሰሜን ሸዋ ዞን በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ከአዲስ አበባ 265 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ብርሃን 135 ኪሎ ሜትር፣ ከመሃል ሜዳ ከተማ 22ኪሎ ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።
ከባሕር ወለል በላይ ከ3200 እስከ 3700 ሜትር በኾነ ከፍታ ላይ ይገኛል። 7800 ሄክታር መሬት ስፋት አለው። ባለፉት 400 ዓመታት በባሕላዊ ሕጎች ሲጠበቅ እና ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ፣ ተፈጥሯዊ ገጽታውን ጠብቆ የሚገኝ ድንቅ ሥፍራ ነው። ጥብቅ ሥፍራው ስያሜውን ያገኘው በአካባቢው በብዛት ከሚበቅለው “ጓሳ” ከተባለው የሳር አይነት እንደኾነ ይነገራል።
በውስጡም ወርቃማው ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮ ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ 14 የሚኾኑ ብርቅዬ አእዋፋት እና በርካታ ሀገር በቀል የደጋ ዕጽዋት እንደሚገኙበት ይነገራል። የምስሀል ማርያም የአርኪዮሎጂካል ሥፍራ እና የሕንፃ ፍርስራሽ፣ የኪዳነ ምኅረት ገዳም፣ ትክል ድንጋዮች፣ ባሕላዊ ክዋኔዎች እና የማኅበረሰቡ አለባበስ በጥብቅ ሥፍራው ዙሪያ ከሚገኙት የቱሪስት መስህቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
መንዝ ጓሳ የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ 45 አባላት ባሉት 45 ሺህ ሕዝብ የወከሉ የጓሳ ምክር ቤት እና በኢኮ ቱሪዝም ማኅበር ቦርድ ይተዳደራል፡፡ ከአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከብዝኀ ሕይወት ሀብቱ በተጨማሪ በማራኪ መልክዓ ምድሩ፣ በሕዝቡ ባሕላዊ አመጋገብ እና አለባበስ ምክንያት መንዝ ጓሳ ለጎብኝዎች ደስታን የሚሰጥ እና የማይረሳ ትዝታን የሚያጎናጽፍ ምድር ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን