ኑ የልደት በዓልን በላሊበላ በጋራ እናክብር!

0
277

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ድንቅ ምድር ናት፤ እርሷን ለማየት የሚጓጉ ሁሉ ለዘመናት ተመላልሰውባታል። ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳት ውብ ሥፍራዎች፣ አበውና እመው የሠሯቸው ረቂቅ አሻራዎች፣ ለዘመናት ተጠብቀው የኖሩ ባሕልና እሴቶች ባለቤት ናት። በውኃ ላይ ገዳም ገድመዋል። በዓለት ላይ ደብር ደብረዋል። ከዓለም የቀደመና የረቀቀ ታሪክ ጽፈዋል። ከረቀቁ ጥበቦቻቸው መካከል ዓለት እንደ አሽከር አዝዘው የሠሩት ጥበብ አንደኛው ነው።

የኢትዮጵያውያን ድንቅ እጆች እና ብሩህ አዕምሮዎች ጥበብን ያሳረፉበት፣ ስጋና መንፈስ የተዋሃዱበት፣ ሰማይና ምድር የተገለጡበት፣ ጥበብ እና ሃይማኖት የጸኑበት፣ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ከጣሪያ ወደ መሠረት የተዘረጋበት ሕያው ሥፍራ ነው። ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ በዓለት ብራና ሕያው ታሪክን የጻፉበት መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቦታ ነው ቅዱሳ ላሊበላ።

ይሕ ድንቅ ስፍራ የዓለም ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አንድ ምክንያት ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል። በየዓመቱ እልፎችን ከኢትዮጵያ ጋር አስተዋውቋል። በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላሊበላ የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ለዓለም እያሳዩ እስካሁንም ዘልቀዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ከዘመኑ የሕንፃ ግንባታ ተለይተው፣ ድንቅ በኾነ ጥበብ የተፈለፈሉ ናቸውና አሁንም ድረስ እጹብ እየተባሉ ይኖራሉ።

የኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጣኔና የላቀ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ማሳያ የኾኑት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1970 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ባሕል እና ሳይንስ ተቋም (ዬኔስኮ) የዓለም ቅርስ ኾነው ተመዝግበዋል። የዓለም ቅርስና የሀገር ሃብት የኾኑት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎብኝዎችና አጠቃላይ ከቱሪዝም ዘርፉ ከሚገኝ ገቢ ኑሯቸውን የሚመሩባቸው ለስጋም ለነፍስም የተመቹ ናቸው።

በላሊበላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ በተከሰተው የሰላምና ጸጥታ ችግር የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጎድቶ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገው ዘልቀዋል። ለቅዱስ ላሊበላ የቱሪዝም መነቃቃት ተስፋው በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን የሚከበረው የልደት በዓል ነው። የልደት በዓል በላሊበላ ከሌላው ዓለም ሁሉ ይለያል። የበዓሉ አከባበር ሃይማኖታዊ ክዋኔም ውብ እና ደማቅ ነው። የቤዛ ኩሉ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓትም በላሊበላ ብቻ የሚከወን መኾኑ ከበዓሉ ድንቅ ገጽታዎች አንዱ ያደርገዋል።

የዘንድሮው የልደት በዓል አምሮና ደምቆ በቱሪስት ተጥለቅልቆ እንዲከበር የላሊበላ ወጣቶች እየሠሩ ነው። ይህን ሀሳብ እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ካሉ ወጣቶች መካከል የላሊበላ ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ኃይለኢየሱስ አስራደ ይገኝበታል። አስተባባሪው ወጣት ኃይለኢየሱስ አስራደ እንደነገረን የሚመጡ እንግዶችን እግር አጥቦ ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል። የመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም፣ ደጋግመው እንዲመጡ ለማድረግ እየሠራን ነው ብሏል። የከተማዋ ወጣቶች ይህን ሥራ በበጎ ፈቃደኝነት እንደሚከውኑትም ተናግሯል።

በርካታ ምዕመናን የልደት በዓልን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ላሊበላ በእግራቸው ይጓዛሉ የሚለው ወጣቱ ዳገቱን ወጥቶ፣ ቁልቁለቱን ወርዶ፣ ሐሩርና ውርጩን ችሎ በእግር እየገሰገሱ ከተቀደሰው ቦታ መድረስ ልዩ በረከት እንደሚያጎናጽፍም አምነው የሚመጡ ሰዎችን ብዙዎች ናቸው ብሏል።

ከአካባቢው ልጆች በተጨማሪ ከአራቱም አቅጣጫ እግር አጥበው እንግዶችን የሚቀበሉ የቅዱስ ላሊበላ ልጆች በርካቶች መኾናቸውን ነግሮናል። የላሊበላ ከተማ ወጣቶች ወደ ሥፍራው የሚመጡትን እንግዶች ለመቀበል ጓጉተው እየጠበቁ እንደኾነም ነው የተናገረው።

የወጣቶቹ አስተባባሪ ወጣት ኃይለኢየሱስ ለሀገር ውስጥ እና ለውጩ ጎብኝ በዓልን አብረዋቸው እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፏል። ኑ በዓልን በጋራ እናክብርም ብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here