ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰቆጣ ከተማ ደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኝበት ስፍራ ልዩ ስሙ ‘ውቅር አባ ዮሐንስ’ ይባላል፡፡
ይህ የሕዝብ ሀብት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ከ514 እስከ 529 ዓ.ም ባሥተዳደሩት የአጼ ካሌብ ዘመነ ንግሥና ነው የተገነባው።
ውቅር መስቀለ ክርስቶስ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በ500 ዘመን እንደሚበልጥ የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ። የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቁመቱ 11 ሜትር ከ 60 ሴንቲ ሜትር እና ወርዱ 8 ሜትር ከ55 ሜትር ሴንቲ ሜትር እንደኾነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍሎ እና ተጠርቦ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ በሦስቱም ጎኖቹ ከተፈለፈለበት ቋጥኝ ተለይቶ የቆመ ነው፡፡ በምዕራብ በኩል ግን ጣራው ከቋጥኙ ጋር ተያይዟል፡፡ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ሰባት ክፍሎች፣ አራት በሮች፣ አምስት ደረጃዎች፣ 14 ዝግ እና ክፍት መስኮቶች እንዲኹም 11 አምዶች ያሉት ጥንታዊ እና ማራኪ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ የአጼ ካሌብ እና የልጃቸው ገብረ መስቀል የክብር ዕቃ ማስቀመጫ እና የዋግ ሹሞች መቃብር እንደነበረ ይነገራል፡፡ አስክሬንን አድርቆ በማስቀመጥ ጥበብ ተዘጋጅተው ለረዥም ዘመናት እንደተቀመጡ የሚነገርላቸው የበርካታ ሰዎች አካላት በቤተክርስቲያኑ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አስከሬኖቹ የተገነዙት በቆዳ ኾኖ ቆዳዎቹ በትናንሽ እንጨት መሰል ቁልፎች እንዲያያዙ ተደርጓል፡፡
በጥንታዊ ዘመን አስከሬንን አድርቆ የማስቀመጥ ጥበብ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ኢትዮጵያዊያን ምስክሮቻቸው በውቅር መስቀለ ክርስቶስ ለረጅም ዘመናት በቤተ ክርስቲያኑ ምዕራባዊ አቅጣጫ የተቀመጡት ቅሪት አካላት ናቸው፡፡ እጅግ ድንቅ እንደነበሩ አሻራቸው የሚመሰክረው ውብ የስዕል ሥራዎች ዛሬ ላይ በዘመን ቆይታ እና በጥንቃቄ ጉድለት ደብዛቸው ሊጠፋ ተቃርበዋል፡፡
ከ1ሺህ 526 ዓመታትን በላይ ቆሞ ታሪክን የሚዘክረው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ በ1951 ዓ.ም ሙያዊ ጥናት ያልተጨመረበት ጥገና ከማግኘቱ ውጭ አስታዋሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ በመስቀለ ክርስቶስ የሚገኙትን ስዕሎች ለመረዳት እንደሚቻለው የአሳሳሉ ጥበብ ጥንታዊውን ዘዴ የተከተለ ነው። ስዕሎቹ የተሠሩት በጭቃ ሞርታር ግድግዳው ላይ በተለፈጠ ጨርቅ እና በውቅር ሕንፃው ላይ በተቀባ የኖራ ቀለም ላይ ነው፡፡
ስዕሎቹ የውኃ ቀለም እና የቀለም ቅብ ሥራዎች ናቸው። በመስመሮች የነገሮችን እና የገጾችን ተምሳሌነት የሚያሳዩ የወዝ ሥራዎችም ይታይባቸዋል፡፡ በእነዚህ የአሳሳል ዘዴዎች የተሠሩት ስዕሎች በቤተክርስቲያኑ ደጀሰላም ግድግዳ ላይ በመግቢያው በር እና በቋሚ ምሰሶዎች ላይ ይታያሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!