“ከተፈጥሮ የተገኘው የጥበብ ካባ”

0
73

 

“ዝናቡ ላይዘንብ እያጉረመረመ፣
ልቤ ገሳ ለብሶ ከደጅሽ ከረመ…” ተብሎ ተዚሞለታል። ክረምት ሲመጣ በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የዝናብ እና የብርድ መከላከያ የኾነው “ገሳ” የብዙዎች መጠለያ ነው።

ይህ ጥንታዊ የዕደ-ጥበብ ውጤት አርሶ አደሮች እና እረኛው ከእርሻ መሳሪያቸው ጋር አዋሕደው የሚጠቀሙበት የዕለት ከዕለት ሕይዎት መገለጫም ነው።

​ገሳ በዋነኛነት በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሚኖሩ እረኞች እና አርሶ አደሮች ከቄጤማ (ከሳር መሰል ተክል) የሚሠሩት ባሕላዊ የዝናብ እና የብርድ መከላከያ ልብስ ነው። ይህ ጥንታዊ መገለጫ የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት የሚደግፍም ነው።

​ገሳ የሚሠራው ቄጤማን በማስተሳሰር እና በልዩ የዕደ-ጥበብ ክህሎት እንደ ካባ (ካፖርት) በመስፋት ነው። አሠራሩ ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ ትከሻ ላይ በሚንጠለጠል መልኩ ይዘጋጃል፤ ዝናብ እና ውርጭን ለመቋቋምም ያስችላል።

ከጥንካሬው የተነሳ በድንጋይ፣ በቁጥቋጦ እና በእሾህ መካከል በሚደረግ እንቅስቃሴ አይቀደድም፤ ይህም ከብቶችን ለሚጠብቁ እረኞች እጅግ ተመራጭ ያደርገዋል።

​ገሳ የሚዘጋጅበት ጥሬ እቃ የዝናብ ጠብታ ወደ ውስጥ ዘልቆ እንዳይገባ የመከላከል ከፍተኛ ችሎታ አለው። የውፍረቱ መጠንም ኾነ የአሠራር ዘይቤው ሰውነትን ብርድ እንዳያገኘው እንዲከላከል ተደርጎ ነው የሚዘጋጀው።
የሰውነት ሙቀትንም ይዞ እንዲቆይ የማድረግ ኃይል አለው።

​የጓንጓ ወረዳ ነዋሪው መርጌታ ልዑል ኃይሉ ገሳ በተለይ ክረምት ሲመጣ በአካባቢያቸው የተለመደ እንደነበር ነግረውናል። የሚዘጋጀውም ከወንዝ እና ረግ ረግ ቦታ በሚበቅለው ቄጤማ ነው ይላሉ። ይህ ባሕላዊ የዝናብ መከላከያ በአካባቢያቸው በቄጠማ ብቻ ማኅበረሰቡ ከአባቶቹ በወረሰው ጥበብ እንደሚሠራውም ገልጸዋል።

​ገሳ በተለይ ክረምት ለዝናብ እና ብርድ መከላከያ በጣም ያገለግላል ነው ያሉት። በጥንት ጊዜ ጥላ በማይኖርበት ሰዓት ሩቅ ሀገር መንገድ ለመጓዝ ነጋዴዎች ይጠቀሙበት ነበር ብለዋል።

አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሰብላቸውን ከወፍ ለመጠበቅ ሲሉ በማሳው አካባቢ እንደ ቤት አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበርም አንስተዋል።

ይህን ባሕላዊ የዝናብ እና የብርድ መከላከያ ገሳ አሁን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ አለመኾኑን ትዝብታቸውን ነግረውናል። እርሳቸው ግን ለልጆቻቸው ለማውረስ ሠርተው ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።
ጥበቡ ለነገው ትውለድ እንዲሻገር ማድርግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ገሳ የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የባሕል አሻራ ነው። እረኛው ከተፈጥሮ በሚያገኘው ግብዓት የዕለት ከዕለት ችግሩን መፍታቱ ለዘመናት የኖረ የአኗኗር ዘይቤው መገለጫ ነው። ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ባሕላዊ ጥበብ የሚገኝ ቢኾንም ዕደ-ጥበቡን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ቢሠራ ሲሉም መክረዋል።

#አሚኮ_ዜና #TraditionalCraft
#Gesa #ክረምት

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_13_2018ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here