ክረምት እና የልጅነት ትዝታ!

0
86

 

የማይተካ፤ መልሶ የማይገኝ፤ ልብን በትዝታ የሚያናውጥ፤ ሲያስታውሱት በትዝታ ባቡር የሚያንሳፍፍ፤ ወደ ኋላ የሚመልስ የደስታ መግነጢሳዊ የመሳብ ኃይል አለው የልጅነት ጊዜ።

በቴክኖሎጂ ዘመን ያደጉ የዛሬዎቹ ሕጻናት አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በዲጂታል መተግበሪያዎች እና በቤት ውስጥ ጨዋታዎች በመኾኑ የዚያን ጊዜውን የደስታ እና የፍቅር የልጅነት ጊዜ ቢነገራቸው ላይረዱት ይችሉ ይኾናል።

በዚያ ዘመን ቀኑ በነጎድጓድ እየታረሰ፤ ጥቁር ዳመና ያዘለው ሰማይ ዶፉን እያወረደ፤ ቤተሰብ በእሳት ዙሪያ ተሰብስቦ ቆሎ እየተበላ፤ ከእሳቱ የሚወጣው ጭስ ዓይኖቻችንን እንድናሽ እያስገደደ፤ ጥርሶች በጨዋታ ሲፈኩ የዝናቡን ድምጽ፣ የጣሪያው ቆርቆሮ በዜማ ሲያጮኸው፤ በሕጻን እጆቻችን ጆሯችንን ሸፍነን” ሿ ሿ” የሚለውን ድምጽ እየሰማን የዝናቡን ማባራት በትዕግሥት እንጠብቃለን።

የዝናቡን ማባራት ተከትሎ በሩጫ ከጓደኞቻችን ጋር ተጠራርተን የልጅነት ወዛችን፤ የነጻነታችን መገለጫ፤ የአብሮነታችን ምንጭ፤ የመተባበራችን ማሳያ፤ የፈጠራ ክህሎታችንን ለማሳየት ወደ ጭቃ ማቡካት ጨዋታችን እንሰየማለን።

ሸርተቴ ሠርተን በመውደቃችን እየሳቅን ደግመን እንነሳለን፤ ደግመን እንወድቃለን ደግሞም እንነሳለን፤ ጭቃ አድቦልቡለን ድስት፤ መኪና፤ ቤት፤ ግድብ እና ሌሎችንም ቅርጻ ቅርጾች እንሠራለን።

ከጭቃ የሠራነውን ድስት መሰል ቅርጽ እያፈነዳን “ዷዷሽ” እንጫወታለን፤ ልብሳችን በጭቃ ተበላሽቶ፤ የፊት ገጻችን በጭቃ ተቀብቶ፤ በንጹሕ ልብ፤ በደግነት፤ በፍቅር ተጫውተን አልፈናል።

አንዱ ጭቃ ሲያቦካ፤ ገሚሱ ውኃ ሲያቀብል፤ ከፊሉ ግድብ ሢሠራ፤ ግማሹ በጭቃ ድብድብ ሲገጥም፤ እናቶች የልጆችን ልብስ መባለሸት ተመልክተው ለመቆጣት ሲፈጥኑ፤ ሕጻናት በኅብረት ሲሮጡ፤ አኩኩ፤ ሌባ እና ፖሊስ ጨዋታ እና ሌሎች ጨዋታዎችን የልጅነት ድንቅ ትዝታዎች ናቸው።

ይህ የልጅነት ጊዜያችን የአብሮነት፤ የመተባበር፤ የመደጋገፍ፤ የመቻቻል ማኅበራዊ እሴቶቻችን የምናሳድግበት ድንቅ ጊዜ ነበር። ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት የበርካታ ልጆች የፈጠራ ክህሎት መነሻ፤ የስኬታቸው ሀሁ፤ የራዕያቸው መጸነሻም ነው።

በልጅነት ጊዜ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ብሎ መከፋፈል የለም ብቻ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሽከርከር፤ በጋራ መብላት፤ በጋራ መካፈል፤ አንዱ ለአንዱ ጠበቃ መኾን የልጅነት ጊዜ የገነባንበት ትዝታችን ነው።

በኮልታፋ አንደበት የእናት ሀገርን መዝሙር መዘመር፤ እምዬ ኢትዮጵያ የልጅነቴ ዓለም ብሎ ደጋግሞ መጥራት ያ ድንቅ የልጅነት ጊዜ ነበር።

ክረምት የልጅነት ማስዋቢያ፤ የስብዓና ትምህርት ቤት፤ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነት፣ የንጹሕ ልብ መሠረት፤ የራዕይ መሰነቂያ፤ የፈጠራ መለማመጃ ክረምት የሕጻናት ዓለም መሠረት ነው።

ያ ውብ ጊዜ፤ ያ ልጅነት፤ ያ ትውስታ፤ ያ ነጻነት ዛሬም እንደ አዲስ ሲተረክ በልባችን ውስጥ የፍቅርን ትዝታ ይቀሰቅሳል።

የእርስዎ የልጅነት የክረምት ጊዜ ምን ይመስል ነበር? ትዝታዎን💬 ያጋሩን👇👇

#አሚኮ #ክረምት_እና_ልጅነት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር#ሐምሌ_17_2018 ዓ_ም

በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here