ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን እምብርት ላይ የሚገኘው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከተራ ተፈጥሯዊ መጠለያነት በላይ የሕይወት፣ የጥበብ እና የውበት ማሠሪያ ድልድይ ነው።
ከደባርቅ ከተማ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ አስደናቂ ስፍራ በዓለማችን ብርቅዬ የኾኑት የዋሊያ፣ የቀይ ቀበሮ፣ የምኒልክ ድኩላ እና የጭላዳ ዝንጀሮዎች መነኻሪያ ብቻ ሳይኾን የእንስሳቱ አስገራሚ ማኅበራዊ ሕይወት ጎልቶ የሚታይበት ታላቅ ምስጢርም ነው።
አቶ ላቀው መልካሙ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተወካይ ኀላፊ ናቸው። እነዚህ እንስሳት ልክ እንደ ሰዎች የየራሳቸው ማኅበረሰብ፣ የቤተሰብ ሕግ እና የሚደንቅ የአብሮነት ጥበብ አላቸው ይላሉ።
ጭላዳ ዝንጀሮዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የአንዱን ፀጉር አንዱ በማጽዳት እና በመንከባከብ ነው ብለዋል። ይህ ለእነሱ የፍቅር እና የአብሮነት መግለጫቸው እንደኾነም አጫውተውናል።
በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር እንኳን በሰላማዊ መንገድ በድምጽ እና በፊት ገጽታ ይወያያሉ፤ ይስማማሉ ነው ያሉት።
በዱር እንስሳት ሕግ ውስጥ አንደኛው አዳኝ፤ ሌላኛው ደግሞ ታዳኝ መኾን የተለመደ የተፈጥሮ ዑደት ቢኾንም በእነዚህ ብርቅዬ ፍጡራን መካከል ግን የማይነካኩ የመኖሪያ ስምምነቶችን የተፈራረሙ ይመስላል ነው ያሉት።
ዋሊያ የጭላዳ ግልገሎችን በጭራሽ አይነካም፤ ጭላዳዎቹም ዋሊያውን አያባርሩትም። እርስ በእርስ እየተከባበሩ በፍቅር እና በሰላም አብረው ይኖራሉ።
የዋልያ የሕይወት ዘይቤም ከጭላዳዎች ጋር የተሳሰረ ነው ብለዋል። ይህ መስተጋብር ደግሞ እንዲሁ ጎረቤት የመኾን ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሕልውና ጭምር እንጂ! ይላሉ የፓርኩ ተወካይ አቶ ላቃቸው።
ጭላዳዎች አካባቢያቸውን በመቃኘት ረገድ እጅግ ንቁ ናቸው። እንደ ነብር ያሉ አጥቂ እንስሳት ድንገት ሲመጡ ጭላዳዎች ልዩ የኾነ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ድምፅ ያሰማሉ።
ዋሊያ ይህንን የጭላዳዎች የጭንቀት ጩኸት በመስማት ራሱን እና መንጋውን ከአደጋ ይከላከላል ብለዋል።
ለዚህም ነው የዋሊያ እናቶች ግልገሎቻቸው በጭላዳ መንጋዎች መሃል አብረው እንዲውሉ የሚፈቅዱት ነው ያሉት።
ጭላዳዎቹ ለዋሊያ ግልገሎች ነጻ ጥበቃ የሚያደርጉ “የሰላም አስከባሪዎች” ናቸው ማለት ይቻላል።
የስሜን ተራራዎች ተፈጥሯዊ ውበት ብቻ ሳይኾኑ ፍጥረታት ተደጋግፈው እና ተከባብረው እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩበት ሕያው የሕይወት መድረክም ጭምር ናቸው።
#አሚኮ #ሰሜን-ተራራዎች #ድንቅ ተፈጥሮ #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰአሚኮ_ዜናብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !









