በሰሜን ሽዋ ዞን የደብረ መንክራት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም (ሸንኮራ ዩሐንስ) ዓመታዊ የንግሥ በዓል ነገ ይከበራል።
📌የገዳሙ መገኛ:-
ገዳሙ በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ይገኛል። ከአዲስ አበባ 144 ኪሎ ሜትር፣ ከወረዳው ዋና ከተማ አረርቲ ደግሞ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። 🚗🗺️
📌ታሪካዊነቱ:-
በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ የሚነገርለት ገዳሙ በሚሰጠው የፈዋሽነት ፀበል፣ በጥንታዊ ቅርሶቹ እና ማራኪ በኾነው ተፈጥሯዊ ገጽታው በዞኑ ካሉት ከቀዳሚዎቹ የሃይማኖታዊ ቱሪዝም መዳረሻዎች ይመደባል።🏞️
📌የበዓሉ አከባበር ፦
በዓሉን ለመታደም ከየአቅጣጫው የሚመጡ መንፈሳዊ ተጓዦች በፈለገ ሕይወት ከተማ በመሠባሠብ እጅግ ማራኪ በኾነ መልክዓ ምድር መካከል ከሚፈሰው የሸንኮራ ወንዝ ስር ወደሚገኘው የፀበል ቦታ በሰልፍ እየተጓዙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ይከውናሉ። 🎊🌊
የንግሥ በዓሉም በርካታ ቁጥር ያላቸው አማኞች እና ሊቃውንተ ቤተክርስትያን በተገኙበት በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚከበር ነው።🕯️
📌የእንግዳ አቀባበል ዝግጅት :-
የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው እንደገለጹት የሸንኮራ ዩሐንስ በከፍተኛ ቁጥር የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን የሚያስተናግድ ሃይማኖታዊ መዳረሻ ነው። 📈
የዘንድሮውን የንግሥ በዓል ለማክበር ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ከአራት ቀናት በፊት ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አማኝ ወደ ገዳሙ መግባት እንደጀመሩ መምሪያ ኀላፊዋ አረጋግጠዋል። 🚌⛺
እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የዞኑ እና የወረዳው አሥተዳደር ከወጣቶች እና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ኀላፊዋ ጠቁመዋል።
📌የሃይማኖታዊ መዳረሻዎችን የማስፋት ሥራ :-
እንደ መምሪያ ኀላፊዋ ማብራሪያ በዞኑ የሚገኙትን ሸንኮራ ዩሐንስ ገዳምን ጨምሮ የሳማ ሰንበት፣ የጻድቃኔ ማርያም፣ ዘብር ገብርኤል እና አንኮበር ሚካኤል ያሉ ታላላቅ የሃይማኖት መዳረሻዎችን የመሠረተ ልማት ለማሻሻል በሰፊው እየተሠራ ይገኛል። 🛣️🚰
#አሚኮ #ሸንኮራ_ዩሐንስ ሰሜን_ሸዋ #Amhara #NorthShewa #ReligiousTourism 🇪🇹⛪🎉
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
#ባሕር_ዳር፡ ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









