በኢትዮጵያ ብዙ መንደሮች ውስጥ ማለዳ የሚሰማው ያ ሽው… ሽው… የሚለው የእንዝርት ድምፅ ትዝ ይላችኋል?
ይህ ድምፅ ተራ የዕለት ከዕለት ሥራ ብቻ አልነበረም። የሀገርን ባሕል፣ ፍቅር እና ማኅበራዊ ትስስር የሚተርክ ሕያው ጥበብ እንጂ።
እናቶች በተረት፣ በምሳሌ እና በውብ እንጉርጉሮ እያዋዙ ጥጥ የሚፈትሉበት፣ ሕጻናት ልጆቻቸውን በጉያቸው አቅፈው የትውልድ ሥነ ምግባር እና ዕውቀትን የሚያሸጋግሩበት ልዩ መድረክም ነው። ሀገሬው ጥጥ ፈተላን የሴቶች አንድ የሙያ መለኪያ መሥፈርት ያደርገውም ነበር።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑ እናት “ቀጭን ፈትላ የትዳር አጋሯን ጋቢ ያላለበሰች ሴት ምኑን ሴት ኾነች? ይባል እንደነበር ትዝታቸውን አጋርተውናል። እርሳቸውም ትናንትን ሳይተው ዛሬም ላይ አምጥተው ይህንን ጥበብ ከሌሎች ሥራዎቻቸው በተጨማሪ ለዕለት ጉርስ መሸመቻ ይኾናቸው ዘንድ የገቢ ምንጭ አድርገውታል።
አሁን ላይ በባሕላዊ መንገድ ብዙ ጥጥ የሚፈትሉ እናቶችን እየተመለከቱ እንዳልኾነም ትዝብታቸውን አጋርተውናል። አማራጭ አጥቼ እንጂ እኔም አይኔ እየደከመ ነው ብለውናል። ባሕሉ አሁን ላይ እየጠፋ መኾኑ ግን እንዳሳዘናቸው ገልጸውልናል። ሂደቱ አድካሚ እና በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ ባይኾንም በራስ ጥበብ መድመቅ የሚሰጠው የደስታ ስሜት ግን ከፍተኛ ነው ይላሉ።
በአዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ” ባሕላዊ የእጅ ሽመና እና ፈተላ ዘርፍ ግምገማ” በሚል ርዕስ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በባሕላዊው እንዝርት የሚከናወነው ጥጥ ፈተላ እጅግ አድካሚ እና በአንድ ቀን የሚመረተው የክር መጠን በጣም አነስተኛ በመኾኑ የኢንዱስትሪዎች ፍላጎትን ማሟላት እንዳልተቻለ ነው የሚያሳዩት።
በዋጋ ዝቅተኛ እና ዘመናዊ የሚባሉ የፋብሪካ ክሮች ገበያውን በመቆጣጠራቸው የእጅ ፈተላ ዋጋ እንዲቀንስ እና እናቶች ለድካማቸው የሚመጥን ገቢ እንዳያገኙ እንዳደረጋቸውም ጥናቶቹ ይጠቁማሉ። ወጣቱ ትውልድ ይህንን አድካሚ እና ረጅም ጊዜ የሚወስድ ጥበብ የመውረስ ፍላጎቱ እየቀነሰ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጥናት እንዳረጋገጠው የእንዝርትን ድካም የሚቀንሱ እና ምርታማነትን እስከ አራት እጥፍ የሚያሳድጉ በእግር (በእጅ )የሚሠሩ አነስተኛ ባለብዙ ዘንግ የፈተላ ማሽኖችን ለእናቶች ማቅረብ አንዱ እየተወሰደ ያለ መፍትሔ ነው።
የቀደሙ እናቶች ያላቸውን የፈተላ ጥበብ፣ ስልቶች እና ዜማዎች በምስል፣ በድምፅ እና በጽሑፍ መዝግቦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍም ሌላኛው እንደኾነ ተቀምጧል። ደላሎችን በማስቀረት እናቶች የሚፈጥሩትን ክር በቀጥታ ከባሕል አልባሳት ዲዛይነሮች እና ከሚሸምኑ ሰዎች ጋር የሚያገናኝ ሥርዓት መዘርጋትም ያስፈልጋል።
በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ውስጥ በጥበቡ ዙሪያ ወጣቶችን የሚያሳትፉ ሥልጠናዎችን ማስፋፋትም ሌላኛው ነው።
እናቶቻችሁ ወይም አያቶቻችሁ ሲፈትሉ የሰማችሁት የፈተላ ዜማስ አለ? በኮሜንት አጋሩን!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









