“የክረምት ውበት እና የበዓላት በረከት በአማራ ክልል”

0
74

 

በጋው አልፎ ክረምቱ ሲተካ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ጭጋግ እና ብርዱን መፍራት፣ ዝናብ እና ጭቃውን መጥላት ብሎም ከቤት ከመውጣት ይልቅ ቤት መዋል የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። ዳሩ ካለን የዕለት እንጀራ መዋተት ምክንያት ቤት ለመዋል የሚያስችል ምቾትም ድሎትም ባይኖረብም።

ኾኖም በአማራ ክልል የክረምት መምጣት የዶፍ ዝናብ ወሬ ብቻ አይደለም፤ ልዩ አጋጣሚን፣ በረከትን፣ ማኅበረሰባዊ እና ባሕላዊ እሴትን ይዞ የሚመጣ ድባብ እንጂ።

ክረምት በአማራ ክልል አዝዕርት ከመበተን እና ቡቃያና እሸት ከመጠበቅ ባለፈ ማኅበረሰባዊ መስተጋብር የሚጠናከርበት፣ ባሕል የሚደምቅበት እና እምነት፣ ማኅበረሰብ እና ባሕል የሚተሳሰሩበት ልዩ ድባብ ነው።

በዚህ የክረምት ወቅት በክልሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን መሠረት ያደረጉ በዓላት ይከበራሉ። እነዚህ በዓላት የኅብረተሰቡን መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ከማጎልበት ባሻገር የክልሉን የቱሪዝም እና የንግድ እንቅስቃሴ በመዘወር በኩልም ሚናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።

📌 የቡሄ (ደብረ ታቦር) በዓል እና የአካባቢ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት፦

በነሐሴ ወር አጋማሽ የሚከበረው የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በተለይም በደብረ ታቦር ከተማ እና በአካባቢው በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በዓሉን ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍ ስለሚል የገቢ ፍሰቱም በዚያው ልክ ያድጋል። በዓሉ ከሃይማኖታዊ መስተጋብር አልፎ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

📌 የሻደይ/አሸንድየ/ሶለል በዓል እና የቱሪዝም ገቢ፦

በነሐሴ ወር መጨረሻ በላሊበላ፣ በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ኽምራ እና በሌሎች አካባቢዎች በደመቀ ሁኔታ የሚከበር የሴቶች እና ልጃገረዶች በዓል ነው። ይህ በዓል ለሴቶች ተሳትፎ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ነው።

በዓሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን የሚስብ በመኾኑ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እና ለባሕላዊ አልባሳት አቅራቢዎች ትልቅ የገበያ ዕድል ይፈጥራል።

📌 የእንግጫ ነቀላ (ከሲ አጨዳ) ባሕላዊ ሥርዓት እና የአካባቢ ገበያ እንቅስቃሴ፦

በተመሳሳይ በነሐሴ ወር መጨረሻ በጎጃም እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ልጃገረዶች እንግጫ በመንቀል ለታላላቆቻቸው እና ለጎረቤቶቻቸው መልካም ምኞት የሚገልጹበት ባሕላዊ ሥርዓት ይከናወናል።

ይህም ኩነት የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚገናኙበትን እና ለበዓሉ የሚኾኑ አነስተኛ የሸቀጥ ገበያዎችን እና የባሕላዊ መስተንግዶ ቁሳቁስ ንግድን የሚያነቃቃ ነው።

📌 የትራንስፖርት እና የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ መነቃቃት

በበዓላቱ ወቅት በርካታ የክልሉ ተወላጆች እና ጎብኝዎች ከየአቅጣጫው ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ስለሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የምግብ እና የመጠጥ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ያገኛሉ።

📌 የአዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) ዋዜማ ዝግጅት እና የግብይት ጭማሪ፦

የክረምቱ ማጠቃለያ እና የፀደይ ማብሰሪያ የኾነው የነሐሴ መጨረሻ እና የጳጉሜን ሰሞን ለእንቁጣጣሽ በዓል የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት ነው። በዚህ ወቅት የቁም እንስሳት፣ የእህል፣ የቅመማ ቅመም እና የባሕላዊ አልባሳት ምርቶች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጨምር በክልሉ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ የመነቃቃት አቅም ይፈጥራል።

📌 የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኢንተርፕራይዞች ዕድገት

በበዓላቱ ሰሞን ጊዜያዊ የመስተንግዶ፣ የትራንስፖርት፣ የጽዳት እና የጥበቃ ሥራዎች ስለሚበራከቱ ለብዙ ወጣቶች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። በተጨማሪም የአካባቢ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ዕድል ያገኛሉ።

በአማራ ክልል በክረምት ወቅት የሚከበሩ በዓላት እና ሁነቶች የሃይማኖት እና የባሕል እሴቶች መገለጫ ብቻ ሳይኾኑ የአካባቢውን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ፣ የገበያ ትስስርን የሚያጠናክሩ እና ለአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች የገቢ ምንጭ የኾኑ አስፈላጊ ሁነቶች ናቸው።

#አሚኮ #ቱሪዝም #Ethiopia #CultureAndTourism
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018ዓ_ም

በመሠረት መቅጫ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here