“ማማ” በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች በተለይ በወሎ አካባቢ አርሶ አደሮች በመኸር የደረሰውን ሰብል ከወፎች እና ከሌሎች እንሰሳት ለመጠበቅ በማሳው መሐል ከፍ አድርገው የሚሠሩት አነስተኛ ባሕላዊ የጥበቃ ጎጆ ወይም ማረፊያ ነው።
ከሰብል ላይ አዕዋፍን በድምጽ ጩኸት የሚያባርሩበት የንቃት ግንባርም ነው። ከዚህም ጎን ለጎን አብሮ የሚጠቀሙበት ወንጭፍ የጥበቃው ሌላኛው ታማኝ ጓደኛ ነው።
አርሶ አደሮች የዓመት ጉርሳቸውን ለማግኘት በንቃት የሚጠብቁበት፣ ሃሳብ የሚያፈልቁበት እና ማኅበራዊ ጨዋታዎች የሚደረጉበት የአርሶ አደሮች የጥበብ ምልክት ነው። በዚህች ትንሿ ጎጆ ውስጥ ፍቅር ይፈስሳል፤ በደስታ እና በሰላም ልብ ለልብ የሚወራበት መድረክም ነው።
ማማ ከጥበቃ ባለፈ አርሶ አደሮች ከፍ ባለው ቦታ ኾነው ከርቀት የተለያዩ ሰብሎችን እና ዕጽዋትን እየተመለከቱ ተፈጥሮን የሚያደንቁበት ልዩ ስፍራም ነው።
በደቡብ ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ኀይሉ ታደሰ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ከአዕዋፍ እና ከዱር አራዊት ለመጠበቅ የሚጠቀሙበት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ ከሀገር በቀል ዕውቀት ውስጥ “ማማ” አንዱ ነው ይላሉ። ማማ በተለይም ማሽላን እና የመሳሰሉ ሰብሎችን ከወፎች እና ከተለያዩ እንስሳት ለመከላከል የሚሠራ ነው ይላሉ።
ማማ ትልቅ ወጭን ሳይጠይቅ በሀገረኛ ጥበብ የሚዘጋጅ ሲኾን፤ እስከ ሦሥት ሜትር ከፍታ ሊኖረው ይችላልም ይላሉ። ጠንካራ እንጨቶች፣ የዛፍ ቅርንጫፎች፣ ገመድ ወይም የዛፍ ልጥ እና ሳር በመጠቀም እንደሚሠሩትም ነው ያስረዱት። አርሶ አደሮች እንደ ማሳው ሁኔታ ማማውን መሬት ላይ ወይም ከፍ አድርገው ሊሠሩት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ማማ ከሰብል ጥበቃ ባለፈ ከፀሐይ፣ ከብርድ እና ከዝናብ (በተለይ የበልግ መግቢያ ወቅት ዘግይቶ ሲገባ) ይከላከላል ነው ያሉት። ለአካባቢው ምቹ ዕይታን እና ወንጭፍ ለመጠቀም በሚመች መልኩ ኾኖ ይዘጋጃልም ይላሉ።
ኢትዮጵያ የቀደመች የሥልጣኔ ባለቤት እንደመኾኗ ማኅበረሰቡ ዕለት ከዕለት ኑሮውን ለመምራት ይጠቀምበት የነበረው ይህ የጥንት ጥበብ ዛሬም ድረስ በ አርሶ አደሮች ዘንድ በሥራ ላይ ይገኛል። ማማ የሰብል ጠባቂ ብቻ ሳይኾን የሕይወት፣ የትዝታ እና የባሕል መገለጫም ነው።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









