በጉዳት ላይ የነበረው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ሊጠገን ነው።

0
50
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰቆጣ ከተማ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ቤተክርስቲያኑ በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ485 ዓ.ም እንደተገነባ የውቅር መስቀለ ክርስቶስ ገዳም አገልጋይ እና የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ ቄስ ብርሃነሕይወት እንቁ ባሕሪ ተናግረዋል፡፡
ውቅር መስቀለ ክርስቶስ አሁን ላይ የ1ሺህ 533 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍሎ እና ተጠርቦ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን ቁመቱ 11 ሜትር ከ60 ሴንቲ ሜትር እና ወርዱ 8ሜትር ከ55 ሴንቲ ሜትር እንደኾነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከአንድ ዓለት ተፈልፍሎ የተሰራው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በሦስቱም ጎኖቹ ከተፈለፈለበት ቋጥኝ ተለይቶ የቆመ ሲኾን በምዕራብ በኩል ግን ጣራው ከቋጥኙ ጋር ተያይዟል፡፡
ቤተክርስቲያኑ አምስት ምሰሶዎች፣ 10 መስኮቶች፣ ሦሥት በሮች፣ በውስጡ አራት ክፍሎች እንዲኹም 11 አምዶች ያሉት ጥንታዊ እና ማራኪ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ነው ይላሉ ቄስ ብርሃነሕይወት እንቁ ባሕሪ፡፡
በቤተክርስቲያኑ እድሜ ጠገብ የኾኑ በርካታ የብራና መጽሐፍት፣ የወርቅ መስቀሎች እና የአጼ ካሌብ እና የልጃቸው ገብረ መስቀል የክብር ዕቃ ማስቀመጫም ይገኙበታል፡፡
በወቅቱ የነበሩ ነገሥታትን፣ መሳፍንትን፣ ዋግ ሹሞችን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ደርቆ በጥበብ ተዘጋጅቶ ለረዥም ዘመናት ሳይፈረሰ እና ሳይበሠብሥ በቤተክርስቲያኑ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ ይገኛልም ነው ያሉ፡፡
አስከሬኖቹ የተገነዙት በቆዳ ኾኖ ቆዳዎቹ በትናንሽ እንጨት መሰል ቁልፎች እንዲያያዙ ተደርጓል፡፡
እጅግ ድንቅ እንደነበሩ አሻራቸው የሚመሰክረው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሳሉ የሚነገርላቸው ውብ የስዕል ሥራዎች ዛሬ ላይ በዘመን ቆይታ እና በጥንቃቄ ጉድለት ደብዛቸው ሊጠፋ መቃረቡንም ተናግረዋል፡፡
ይህ ረጅም ዓመታትን ቆሞ ታሪክን የሚዘክረው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ከ50 ዓመታት በፊት ሙያዊ ጥናት ያልተጨመረበት ጥገና ከማግኘቱ ውጭ አስታዋሽ አላገኘም ነው ያሉ፡፡
አሁን ላይም በከፍተኛ ጉዳት ላይ እንደሚገኝ እና የሚመለከተው አካል ጥገና በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባልም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የዋግኸምራ ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ካሳ ከበደ እንዳሉት ቅርሱ በጉዳት ላይ ይገኛል።
ቤተክርስቲያኑ ከ50 ዓመት በፊት ከፍተኛ አደጋ ሲደርስበት በጊዜያዊነት የቅርስ ጥገና ሳይንሱን ባልተከተለ መልኩ በስሚንቶ ጥገና ሊደረግ የተሞከረ መኾኑን በአፈ ታሪክ ሲነገር ይሰማል ያሉት መምሪያ ኀላፊው ከዚያ ወዲህ ምንም አይነት ጥገና አልተደረገለትም ነው ያሉት፡፡
በዚህ ምክንያትም ግድግዳው በመሰንጠቁ እና በዙሪያው ውኃ በማፍሰሱ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጓል፣ በክረምት ወቅትም በጎርፍ እየተሸረሸረ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ለመታደግ በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ጣራ የማልበስ ሥራ የተሠራ ቢኾንም ከጊዜ ብዛት እንጨቱም ጣራውም በማርጀቱ ወደ ውስጥ ውኃ እያሰረገ ሌላ ችግር ኾኖበታል ነው ያሉ፡፡
ቅርሱ የሀገር ሃብት ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ከዚህ በላይ ጉዳት ሳይደርስበት የሚመለከታቸው አካላት ተባብረው ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጥገና ሥራው ቢገቡ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃ እና ልማት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ሀብታሙ አብርሃ እንዳሉት በኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ከምንላቸው ውስጥ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው ፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የቅርሱ ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነት እና እሴት ከፍ ያለ በመኾኑ እና በሀገሪቱ ያሉትን ቅርሶች ከመጠበቅ እና ከመንከባከብ አንጻር ጥገና ለማድረግ ዕቅዶችን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ቅርሱ ካለበት አሁናዊ ጉዳት አንጻር ሂደቱን ጠብቆ በጥንቃቄ መጠገን ስላለበት ከጥገናው ጥናት ጀምሮ እስከ ጨረታው ጊዜ ድረስ ሰፊ ጊዜ ወስዷል ነው ያሉ፡፡
አሁን ላይ የጨረታ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ አልቆ አሸናፊው ተለይቷል ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው አንድ የቅርስ ጥገና ለመሥራት አካባቢያዊ ሰላም ይፈልጋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይም የሀገሪቱ የጸጥታ ችግር በተለይ ቅርሱ ያለበት አካባቢ ሰላም ያለበት መኾኑ ስለተረጋገጠ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በቀጥታ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ ይመቻቻል ነው ያሉ፡፡
ለሥራው አስፈላጊ የኾኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም ተጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት እና የሚዲያ ተቋማት ባሉበት የሥራ ርክክብ እንደሚካሄድም አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ለቅርስ ጥገናው እና ለልማቱ አስፈላጊ የኾነውን በጀት መመደቡንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!c

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here