መታጨትን ለማሳወቅ በንፍሮ ዕደላ የሚጀምረው የራያ ባሕላዊ ሠርግ

0
3
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በራያ ምድር ሠርግ የሁለት ወጣቶች ጥምረት ብቻ አይደለም። የይሉኝታ፣ የክብር፣ የደስታ እና የማኅበረሰቡ የአንድነት መገለጫ ትልቅ ዓደባባይ ጭምር እንጂ።
ከእጮኝነት ጀምሮ እስከ ሠርጉ ማግስት ድረስ ውብ ሥርዓቶች የሚታዩበት ነው። እጅግ ደማቅ፤ በደራ ጨዋታ የጎለበተ፤ በዜማ እና እንጉርጉሮ የተከሸነ፤ በፈጣን የዳንኪራ ምት የታጀበ የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እና ሥነ-ልቦና በግልጽ የሚያሳይም ነው።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የራያ አካባቢ ነዋሪ እንዳጫወቱን የራያ ሠርግ ዝግጅቱ የሚጀምረው ከመተጫጨት ነው ብለውናል። ሴት ሙሽራ እንደታጨች ንፍሮ ተቀቅሎ በሙሽሪት ዕደላ ዘመድ፣ ጎረቤት እና የአካባቢው ሰዎች በጋራ ተሰብስበው ይመገባሉ። ይህም ሙሽሪትን የተመኛት ካለ እንዳያጭ ለማሳወቅ ነው ብለዋል።
ከማጫ በኋላ ልጃችን አስደስቶልናል በሚል ቤተሰቦቿ ለወንድ ሙሽራ ቤተሰቦች ታጋ (ሽልማት እና የቀጣይ የጋራ መተዳደሪያ ንብረት) ይሰጣሉ። ሽልማቱ አልባሳት፣ ገንዘብ፣ መሬት፣ ከብት ሊኾን ይችላል ነው ያሉት።
አቅማቸውን ያገናዘበ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለመንፈሳዊ አባቷ እና መንፈሳዊ እናቷ ስጦታ ይሰጣቸዋል። የክርስትና እናት ሽልማቱን አትጠቀመውም። ከራሷ ጨምራ ለሙሽሪት መዋቢያ እና ገጣጌጥ ገዝታ ትሰጥበታለች። ወንድ ሙሽራም የተለያዩ ስጦታዎችን ለሙሽሪት ይሰጣል።
በሁለቱም ተጋቢዎች በኩል ለሠርጉ የሚኾኑ ዝግጅቶች ሲዘጋጁ ቆይተው ወንዱ ከመረጣቸው ሚዜዎቹ ጋር ጫጉላ ያዘጋጃል። ሴቷ ሙሽራ ደግሞ ከሠርጉ ሦሥት ወይም ሁለት ቀን በፊት እየተጨፈረ እና እየተመረቀች ዘመድ ተሰብስቦ ጥፍሯ ይቆረጣል። ጥፍሯን የሚቆርጠው ቤተሰብ ነው። ይህ የሚኾነው ክፋ መንፈስ እንዳይለክፋት በሚል ነው ብለዋል።
ሙሽሪት እንደ ሌሎቹ አካባቢ ባሕሎች ለሰርጓ ቀድማ ብዙ መዋብ አትችልም። የጋብቻ ሥርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ ወደ ትዳር አጋሯ ቤተሰብ ከሄደች በኋላ ነው የምትዋበው። ይህ የሚኾነው ገና ወንድ ጋር ትውውቅ የሌላት መኾኑን ለማመላከት ነው።
ወንድ ሙሽራ ግን በሰርጉ ቀን ቅቤ ተቀብቶ፣ ስር ኩል ተኩሎ ባሕላዊ አልባሳቱን ለብሶ እና ጫማውን ተጫምቶ ነው የሚሄደው። ዓይኑን መኳሉ በብዙ ሰው ትኩረት እንዳይደረግበት ትኩረት ለመቀየር ነው። በሰርጉ ቀን በሁለቱም ተጋቢዎች ቤት ጎረቤት ዘመድ ተሰብስቦ የተዘጋጀውን ባሕላዊ መጠጥ እየተጎነጨ እና የቀረበውን ማዕድ እየተጋራ ከቆየ በኋላ ጭፈራው ይደራል።
ወንዱ ሙሽራ
“ጀግናው መጣላችሁ ያንበሳው ዝርያ፣
ኮርቶ የሚያስኮራው ሙሽራው ራያ ” እየተባለ ሲወደስ ሴት ሙሽራ ደግሞ
“ቁንጅናሽ ወለባ ጸባይሽ ማር ወለላ፣
ታደለ ያገኘሽ የልታደለ ሌላ” እየተባች ትወደሳለች።
በሴት ሙሽራ ቤተሰብ በኩል ያለው ሁነት ተጠናቅቆ ተመርቀው እንደጨረሱ የቤተሰቦቿን ጉልበት ከሳሙ እና ሽልማት ሲበረከትላቸው ከቆዩ በኋላ በበቅሎ ወደ ወንድ ሙሽራ ቤት ይሄዳሉ። ጭፈራው እና ፉከራው በወንድ ሙሽራ ቤት ይቀጥላል። ዘመድ ጎረቤት ደስታውን ይካፈላል። ምግብ መጠጡም ይቀጥላል።
ከዛም ሙሽሪት ባሕላዊ የራያ ቀሚስ ለብሳና መቀነቷን ታጥቃ በቤተዘመድ ታጅባ ከዳሱ ወጥታ ስትቀመጥ ዘመድ ጎረቤት ከብቧት ይቀመጣል። እየተመረቀች በወተት ታጥባ ጋሜ እና ቁንጮ ትላጫለች። እንሶስላ ትሞቃለች። ቅቤም ትቀባለች። የሠርጉ ቀን ሁነት እንዲህ ደምቆ ያልፋል ከሰርጉ ማግስት ያሉ ኹነቶች ይቀጥላሉ።
ባሕሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ እና እየተበረዘ የመጣበት ሁኔታ ቢኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደነበረበት እሴት እየተመለሰ መኾኑን ባለታሪካችን ነግረውናል።
የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ እንደ ዞን ሠርግን ጨምሮ ሌሎች ባሕላዊ እሴቶች ነባር ሥርዓታቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር እየተሠራ መኾኑን ነግረውናል።
ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠኑ የማድረግ እና የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮችን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here