የአጼ ፋሲል የጥበብ አሻራ ሌላው ማሳያ ሞገዳ !

0
17

 

ባሕር ዳር:ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአለፋ ወረዳ የታሪክ አሻራን አትሞ የቆመ አንድ ድንቅ የጥበብ ውጤት አለ “የሞገዳ” ግንብ።

የወረዳው ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላሹ ደሳለኝ ግንቡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በተለይም በ1638 ዓ.ም በአጼ ፋሲል ዘመነ መንግሥት እንደተሠራ ተናግረዋል።

የሕንጻው አወቃቀር እና የድንጋይ ጥበብ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የአጼ ፋሲልን ቤተ-መንግሥት ያስታውሳል። በተለይም ደግሞ ከአጼ አድያም ሰገድ ዳዊት ደባል ሕንጻ ጋር አስገራሚ ተመሳሳይነት አለው።

የኢትዮጵያ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ማሳያ ኾኖም ዘመናትን የተሻገረው ጥንታዊ ቅርሱ ከሻሁራ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቸባ ሞገዳ ቀበሌ ይገኛል።

የቦታው ቁልቁለታማ እና ዳገታማ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ግንቡ በግርማ ሞገስ ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል።

ጥቁር የተፈጥሮ አለታማ ድንጋይን በኖራ በማያያዝ የተገነባው ይህ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሕንፃ አንድ የምድር ቤት እና አንድ ፎቅ ያለው ነው።

የሕንፃው ርዝመት:-

👉 በሰሜን እና ደቡብ ግድግዳው በአማካይ 8 ነጥብ 23 ሜትር፣
👉 በምሥራቅ እና ምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ 8 ሜትር ይደርሳል።
👉 ውፍረቱ አንድ ሜትር
👉 ቁመቱ 8 ሜትር ገደማ እንደሚደርስ ይነገራል።
ግንቡ በመጀመሪያ የተገነባው ለአካባቢው ባላባቶች እና ነገሥታት መኖሪያ እና ማረፊያነት ታስቦ እንደነበር አቶ መላሹ ገልጸዋል።

ከጊዜ በኋላ የአካባቢው ባላባቶች አንደኛውን ክፍል ለመኖሪያነት ሌላኛውን ደግሞ ለቤተክርስቲያንነት ለመጠቀም በመሞከራቸው ምክንያት ከሕዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። በዚህም ሳቢያ ባላባቶቹ አካባቢውን ለቀው ወደ ጎንደር ከተማ መሄዳቸውን አብራርተዋል። ከዚያ በኋላ ግንቡ ሙሉ በሙሉ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ግንቡ በድርቡሾች ወረራ ወቅት በደረሰበት የቃጠሎ አደጋ ምክንያት አካላዊ ገጽታው በእጅጉ ተጎድቶ ለቤተክርስቲያን ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ሊቋረጥ እንደቻለ ተናግረዋል።

ከዚያም በኋላ አካባቢው ለረጅም ጊዜ ሰው አልባ ኾኖ መቆየቱን ገልጸዋል። ከጊዜ በኋላ የአካባቢው ማኅበረሰብ በዚያው በቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ሌላ አዲስ ሕንጻ በመገንባት ማገልገላቸውን እንደቀጠሉ የቃል ምስክሮች ያስረዳሉ ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ታሪካዊ ቅርስ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተነሳ በመፍረስ እና በመሰንጠቅ አደጋ ላይ ይገኛል ነው ያሉት። ቅርሶች የትናንት የታሪክ ምስክሮች በመኾናቸው ከመጥፋታቸው ለመታደግ መንግሥት ማኅበረሰቡን በማቀናጀት ተገቢውን ጥበቃ እና ጥገና ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ መላሹ አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ

#አሚኮ #ቱሪዝም_ቅርስ #ማዕከላዊጎንደር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here