🌴 ባሕር ዳር የውበት እና የልማት ሕያው ማሳያ !

0
14

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ማዕበል ከሰማያዊው አድማስ ጋር የሚገናኝባት፣ ስመ ጥሩው የዓባይ ወንዝም ተገማሽሮ የሚያልፍባት ውብ ከተማ ናት።

ባለጎፈሬ ዕድሜ ጠገብ ዘንባባዎቿ እና የተንጣለለው የጣና ሐይቅ የውበት ካባን አላብሰዋታል። አጠቃላይ ውበቷ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፈርጥ ከተማ አድርጓታል።

ዛሬ ከተፈጥሮ በረከቷ ባሻገር በታላቅ የልማት እና የለውጥ ጎዳና ውስጥ ኾና አዲስ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።

በሐይቁ ላይ የሚንጸባረቀው የወርቅ ቀለም ያለው የፀሐይ ግባት እና በጢስ ዓባይ ፏፏቴ አካባቢ የሚፈጠረው ቀስተ-ደመና የየትኛውንም ተመልካች ልብ የሚሰርቅ ነው። ይህ ከተፈጥሮ የተቸረችው ውበት እና ድምቀት በነዋሪዎቿ እና በጎብኝዎቿ ልብ ታትሞ ዘመናትን ተሻግሯል።

ምሽት ሲተካ የከተማዋ መብራቶች በሐይቁ ላይ ሲያርፉ ባሕር ዳር የሕይወት ትርጉም የሚታደስባት ከተማ ትኾናለች።

ባሕር ዳር ተፈጥሮ በቸራት ውበት እና በድምቀት ብቻ አልተወሰነችም። በአሁኑ ወቅት የዘመናዊነት እና የዕድገት ማማ ለመኾን እየተጋችም ነው። ከተማዋን ለነዋሪዎቿም ኾነ ለጎብኝዎች ይበልጥ ምቹ፣ ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እግረኛ መንገዶች፤ የብስክሌት መንገዶች፤ የአረንጓዴ ስፍራዎች እና የፓርኮች ግንባታ፤ ዘመናዊ የመብራት ፖሎች እና ያሸበረቁ መብራቶች የከተማዋን ውበት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል። የቱሪስት መዳረሻዎችን የማዘመን ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተሠሩም ይገኛሉ።

በኮሪደር ልማቱ የተገለጠው ጣና እና የመንገድ ዳር ዘንባባዎቿ የከተማዋን ሞቃታማ አየር ወደ ምቹ ቅዝቃዜ ለውጠውታል።

አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፤ የንግድ ማዕከላት፤ የስፖርት እና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች መገንባታቸው የከተማዋን የኢኮኖሚ እና የንግድ ማዕከልነት አልቀውታል።

ባሕር ዳር ሠው እና ተፈጥሮ የተስማማባት ነፍስን የሚያድስ ስሜት ናት። ጠዋት በወፎች ጫጫታ እና በጣና ንጹሕ አየር ሽውታ፤ ከሰዓት በዘንባባዎቹ ጥላ ሼር በእግር መጓዝ፤ አመሻሽ ላይ ደግሞ የዓባይን ሽውታ እየሰሙ በንጹህ ጓዳናዎቿ ዳርቻ ቡና መጠጣት… ይህ ለሰው ልጅ አዕምሯዊ እረፍት እና ለሕይወት መታደስ ትልቅ ስንቅ ነው።

እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ነባር ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ማንነት ሳይበርዝ ይበልጥ አጉልቶ በማውጣት ለሰው ልጅ ሕይወት ምቹ እና ማራኪ አካባቢን እየፈጠረ ይገኛል።

ለመኾኑ የከተማዋ አዲሱ የልማት እና የውበት እንቅስቃሴ ምን ስሜት ፈጠረብዎት?

📲 ሃሳብዎን በኮሜንት ያካፍሉን! 👇

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here