“ሰው ሁሉ በሽታው ራስ ወገቡን ነው፤ የኔስ በሽታዬ ባቲን ነው ባቲ ነው”

0
66

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባቲ ስትነሳ ኅብረ ብሔራዊነት መገለጫዋ ስለመኾኑም አብሮ ይነሳል። የባቲ ከተማ ነዋሪ የኾኑት እና የሀገር ሽማግሌው ሙሐመድአሚን ሰኢድ ባቲ የደጋጎች ሀገር፣ የፍቅር መገለጫ ኾና ለዘመናት የቆየች ከተማ መኾኗን ገልጸዋል።

ሰዎች በአንድነት የሚኖሩባት፣ ለአጎራባች አካባቢዎች ምሳሌ ልትኾን የምትችል የበርካታ ባሕልና ቅርስ ባለቤት ናት ብለዋል።በባቲ ከተማ ባሕላዊ የእርቅና የሽምግልና ሥርዓት ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል ያሉት አቶ ሙሀመድአሚን የመቻቻል እና የፍቅር ከተማ ብለዋታል ባቲን።

በባቲ ከተማ ጥፋት ሲጠፋ፣ ያልተገባ ሥራ ሲፈፅሙ ትንሽ ትልቅ ሳይል በኅብረት በመነሳት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በጋራ በመኾን በመምከር እና በማስተማር ከስህተት እንዲማር ማድረግ የተለመደ ስለመኾኑም አንስተዋል።

በባቲ ከተማ አሥተዳደር የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አደም ሙሐመድ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ የምትገኝው የባቲ ከተማ የተመሠረተችው 1872 ዓመተ ምኅረት እንደኾነ ተናግረዋል።

ባቲ ከሀገራችን ውስጥ ካሉት ትልልቅ ከተሞች ቀድማ እንደተመሰረተች እና የተለያዩ ባሕላዊ እና ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት መኾኗንም ጠቅሰዋል።

ባቲ በድሮው ጊዜ ከጣሊያን ወረራ በፊት የተለያዩ የንግድ መስመሮች እና እንቅስቃሴዎች የነበራት ከተማ ናት። ባቲ ላይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ተከፍቶ እንደነበረ እና በውስጡም የፍየል፣ የበግ እና የከብት ቆዳ ወደ የመን በመላክ ከውጭ ሀገሮች ከየመን እና ከጅቡቲ የተለያዩ ሽቀጣ ሸቀጦች ወደ ከተማዋ ይገቡ እንደነበር ከታሪክ መዛግብቶች ይነገራል ብለዋል።

ባቲ የአፋሩ፣ የአርጎባው፣ የትግሬው፣ የአማራው፣ የኦሮሞው እና የሁሉም ብሔረሰቦች በአንድነት እና በፍቅር የሚገኙባት ከተማ ስለመኾኗም ቡድን መሪው መስክረዋል።

የባቲ የሰኞ ገበያ ከባቲ ከተማ መድመቂያ፣ የአብሮነት እና የአንድነት ተምሳሌት እና ሁሉም በአንድ ላይ የሚገበያዩበት ገበያ ነው።

የባቲ የሰኞ ገበያ ገና ከመድረሱ በፊት ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ ባቲ ከተማ በደማቁ እንግዶቹን ልትቀበል ሞቅ ደመቅ ብላ አምራና ተውባ እንግዶችን ትጠብቃለች።

በዚሁ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ባሕላዊ አለባበሶች፣ ታሪካዊ ዕቃዎች፣ ብሮች፣ ወርቆች፣ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ጭሶች ይቀርብበታል።

ባቲ የመልከ መልካሞች መፍለቂያ፣ የውበት መገለጫ ናት። የባቲ ልጃገረዶች ውበት እና በየአካባቢው የሚሽተው ጭስ የባቲን ውበት ይበልጥ የሚያጎላ ነው ብለዋል።

ባቲ የራሷ የኾነ በስሟ የሚጠራ የሙዚቃ ቅኝት ያላት እና በርካታ ሙዚቀኞችን ያፈራች አካባቢም ናት። ባቲ ውብ እና ማራኪ ከመኾኗ የተነሳ በብዙዎች የውጭ ጎብኝዎች የምትጎበኝ ከተማም ናት።

“ሰው ሁሉ በሽታው ራስ ወገብን ነው፤ የኔስ በሽታዬ ባቲን ነው ባቲ ነው” ብለው ያዜማሉ። ያ ማለት የባቲን ፍቅር ለመግለፅ እና ባቲ የምትናፈቅ መኾኗን ለማመልከትም ነው።

ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here