ሀብታም እና ድሃ እኩል የኾኑበት ተቋም – እድር

0
62
ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሞት በሰው ልጆች ዘንድ ከባድ የመለየት ክስተት ነው። በአጠገብ ያለን ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት፣ የቅርብ ሰው ድንገት ይነጥቃል። የቅርብ ሰው ከጎን ሲለይ ለቋሚ ሰው ሀዘኑ ከባድ ነው። ዙሪያው ገደል ይኾናል፤ ብቸኝነት መጥቶ ድቅን ይላል።
ይህንን ክፉ አጋጣሚ የሚያቃልለው እድር የሚባለው ማኅበራዊ ተቋም ነው። እድር የከበደው ቀለል እንዲል ያደርጋል፤ ያዘነን ልብ ይጠግናል።
እድርተኛም ሀዘንተኛን ለማጽናናት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። አብሮ ደረቱን ይደቃል፤ ቀብሩን ይፈጽማል፤ እዝኑን ያቀርባል፤ ጥዋት ማታ ከድንኳኑ እየተገኘ ሀዘንተኛውን ያጫውታል፤ ሀዘኑን ለማስረሳት ጥረት ያደርጋል።
ታዲያ የሀዘንተኛን ያዘነ ልብ የሚያክም ከእድር በላይ የሥነ ልቦና ተቋም የት አለ?
አባ ታመነ በላይ (አባ ታሜ) የእኛ እድር ጥሩምባ ነፊ ናቸው። ለዚህ ዘገባ ስል አውርቻቸው ነበር። እርሳቸው እንደነገሩኝ በጉልበት ሥራ ነው እድሜያቸውን የገፉት። ጉልበታቸው ሲደክም ነው የእድር ጥሩምባ ነፊ የኾኑት። አንድ አምስት ዓመት የእድር ጥሩምባ ነፍተዋል። በቁጥር ይሄን ያህል ባይሉም የበርካቶችን ዜና እረፍት ለእድርተኛው ‘በሰበር’ አርድተዋል።
በሥራዬ የተረዳሁት ይላሉ አባ ታሜ የእኛ ሰው ድንጉጥ ነው፣ አዛኝ እና ተባባሪ ነው። ልክ መንደር እየዞርሁ እንዳረዳሁት ነጠላውን እያዘቀዘቀ ሀዘን ወደ ደረሰበት ቤት ነው በፍጥነት የሚሄደው።
አባ ታሜ እንደሚሉት የሰውን ሞት እንደቀላል ነገር በጥሩምባ እየለፈፉ መናገር ቢያሳዝናቸውም የሚለፍፉት ለትብብር፣ ለመተጋገዝ መኾኑን ሲያስቡ ደግሞ ይጽናኑበታል። እርሳቸው የጠሩት ሕዝብ የሀዘንተኛውን መከራ ሲያቀልል ሲያዩ ‘እደሰታለሁ’ ነው ያሉት አባ ታሜ።
አቶ ዘለዓለም አበራ ደግሞ በባሕር ከተማ የቀበሌ 10 ቅዱስ ሩፋኤል መረዳጃ እድር ልማት ማኅበር ሊቀ መንበር ናቸው። አሥራ ስድስት ዓመት በአባልነት፣ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ደግሞ የእድራቸው ሊቀ መንበር በመኾን እያገለገሉ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ምንም ሀብት ቢኖርህ፣ ምንም ወገን ቢከብህ ሀዘን ያለ ሰው ትብብር ከባድ ነው።
የእኛ እድር ይላሉ አቶ ዘለዓለም ቀብርን ከማስፈጸም ጀምሮ እስከ አራት ቀናት ድረስ ድንኳን ጥለው፣ በደሽ በደሽ እዝን እያቀረቡ ሀዘንተኛን ያጽናናሉ። የሠፈሩ ሰው ትልቁም ትንሹም ጥዋት ማታ ከድንኳኑ አይቀርም፤ ሀዘንተኞችን ያጽናናል። ታዲያ ይሄ ተግባር ሀዘንተኞች ሀዘናቸውን እንዲረሱ ያግዛል ነው ያሉት አቶ ዘለዓለም።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህሩ ሰለሞን ተሾመ (ዶ.ር) በእድር ማኅበራዊ ፋይዳ ዙሪያ ምሁራዊ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩኝ ደውዬላቸው ነበር። አጋጣሚው ኾኖ ዶክተር ሰለሞን አያታቸውን ቀብረው ሀዘን ተቀምጠው ሳለ ነው የደወልሁላቸው።
“የቤተሰቡ ዋርካ የኾነችውን አያቴን ነው ያጣሁት” አሉ ዶክተር ሰለሞን። ሀዘኑ ከባድ ቢኾንም እድራችን ሀዘናችንን ለማስረሳት የማያደርገው ነገር የለም ሲሉ ነው የነገሩን።
“ታዲያ እኔ ምን የተለየ ምሁራዊ ትንታኔ እሰጥሃለሁ፤ በተግባር እያየሁት ያለውን ነገር ልንገርህ እንጂ” ብለው ከተቀመጡበት ድንኳን ላይ ኾነው ነው ሀሳባቸውን ያጋሩኝ።
እድር እኩልነት የሚረጋገጥበት ማኅበራዊ ተቋም ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን ሀብታም እና ደሃ፣ ትልቅ እና ትንሽ አይለይበትም ይላሉ። የእድር አባላት እኩል መዋጮ ያዋጣሉ፤ በእድሩ እኩል ይገለገላሉ።
እድር ትብብር እና አንድነት ታይበታለህ የሚሉት ዶክተር ሰለሞን ሰው ብቻውን መሸከም የማይችለውን ሀዘን የሚሸከመው እድር ነው። በእድር ውስጥ አንድነት እና መተባበር በግልጽ ይታያል ነው ያሉት።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ እድር ቤተሰባዊነትም ነው። ከልብ መቀራረብን ይፈጥራል። የአንዱ ሀዘን በሌላኛው ላይ ይጋባል። ከሀዘኑም ለመውጣት እንደ ቤተሰብ ይመከርበታል። እናም እድር ከመረዳዳት ባሻገር ነው ብለዋል ዶክተር ሰለሞን።
እውነትም እድር ከመረዳዳት ባሻገር እኩልነት፣ ትብብር እና ቤተሰባዊነት ገዝፎ የሚታይበት ማኅበራዊ ተቋም ነው።
በደመወዝ የቆዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here