ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማ የዓባይ ወንዝ ከሁለት ከፍሏት የሚያልፍ ጣናን በእቅፏ የያዘች ከተማ ናት።
ታዲያ ባሕር ዳር ከተመሠረተችበት ዘመን ጀምሮ ካስፈለጓት ወሳኝ የመሠረተ ልማት አውታሮች መካከል አንዱ ድልድይ ነበር።
ባሕር ዳር በታሪኳ ለሕዝብ ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ እና ለዓባይ ወንዝ መሸጋገሪያነት እያገለገሉ ያሉ ድልድዮች ተገንብተውላታል። ከተማዋን ከቀሪው የኢትዮጵያ አካባቢ የሚያገናኙ ሁለት ድልድዮችን ጨምሮ የከተማዋን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የሚያቀላጥፉ በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ የተገነቡ እና ለነዋሪዎቿ ወሳኝ ጠቀሜታ ያላቸው አነስተኛ የድልድይ መሠረተ ልማቶችም ይገኛሉ።
👉 የመጀመሪያው አላታ ድልድይ ይባላል።
በርግጥ ይህ ድልድይ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣ ብሎ ይገኛል። ጢስ ዓባይ አካባቢ ነው መገኛው። ቀደም ባለው ዘመን የአካባቢውን ነዋሪ በሰፊው አገልግሏል ተብሎ ይታመናል።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወይም ከ1612 እስከ 1626 ዓ.ም አካባቢ በአጼ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግሥት እንደተገነባ ነው የሚነገረው። ድልድዩ ሲገነባ ድንጋዮቹን ለማጣበቂያነት እንቁላል ጥቅም ላይ ውሏል ተብሎ ስለሚታመን “የእንቁላል ድልድይ” የሚል ቅጽል ስምም አለው።
አላታ ድልድይ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ ቅርስ ኾኖ በቱሪዝም መዳረሻነት እያገለገለ የሚገኝ ሲኾን ወደ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ የሚሄዱ ጎብኝዎች ይዝናኑበታል።
👉ሁለተኛው “የዓባይ ወንዝ ድልድይ” የሚባለው ነው።
ይሄኛው በተለምዶ “ነባሩ ድልድይ” ወይም አሮጌው ድልድልይ” እየተባለ ይጠራል። በጥቅምት ወር 1953 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ የሚነገርለት ይህ ድልድይ 225 ሜትር ርዝመት አለው።
ባሕር ዳር ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋች ስትሄድ እና የከተማዋ ምሥረታ ዓባይን ሲሻገር ለከተማዋ ነዋሪዎች መሸጋገሪያ እንዲሁም ከጎንደር እና ከሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች የሚያገናኝ ዋና የመሠረተ ልማት አውታር ነው።
በከተማዋ የሚገኝ ብቸኛ ድልድይ በመኾኑ እና ከ60 ዓመታት በላይ አገልግሎት በመስጠቱ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ከፍተኛ ጫና አርፎበት ነበር።
👉ሦሥተኛው አዲሱ የባሕር ዳር ዘመናዊ ድልድይ ነው።
አዲሱ የባሕር ዳር ዓባይ ዘመናዊ ድልድይ ከተማዋ በፈጣን ዕድገት ላይ በመኾኗ ነባሩ ድልድይ ብቻ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት በቂ ባለመኾኑ በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ተመርቆ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል።
እንደ ክልሉ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ መረጃ አዲሱ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር የጎን ስፋትም አለው።
የአዲሱ ድልድይ ግንባታ ለትራፊክ ክፍት መኾኑ በነባሩ ድልድይ ላይ ያለውን የትራፊክ ጫና እንዲቀንስ አስችሏል። ለውቧ ባሕር ዳር ከተማም ተጨማሪ ውበትን እንድትደርብ አድርጓታል። ግርማ ሞገስ ኾኗትም ይገኛል።
#አሚኮ_ዜና #ቱሪዝም #ባሕር_ዳር #አማራ #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









