ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ የዓለምን ቀልብ የሳበ ድንቅ የቱሪዝም ቦታ ነው። በሌላው ዓለም የማይገኙ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት እና አዕዋፋት የሚገኙበት ብቻ ሳይኾን ለዐይን የሚስቡ በርካታ ተራራዎች፣ ፏፏቴዎች እና በእሳተ ጋሞራ የተፈጠሩ ንብርብር ድንጋዮች የሚገኙበትም ነው።
ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ያቀና ጎብኝ ብርቅዬ እንሰሳትን፣ ራስ ደጀን ተራራን እና ጅንባር ፏፏቴን ካልተመለከተ ጉብኝቱ ስኬታማ ነው ሊባል እንደማይችል ይታሰባል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን እና የዩኔስኮ መረጃ እንደሚያሳየው ጅንባር ፏፏቴ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኝ አስደናቂ ተፈጥሮ ሲኾን ከ500 ሜትር በላይ ርቀት እንዳለው ይነገርለታል። በአፍሪካ ከፍተኛ ርዝመት ካላቸው ፏፏቴዎች መካከልም ይመደባል።
ውኃው የሚያርፍበት ጥልቀት ሩቅ ከመኾኑ የተነሳ የፏፏቴውን መጨረሻ ያዩት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ እንደኾኑም ይነገራል። በተለይ በክረምት ወቅት የሚወርደው ውኃ ስለሚበዛ ፏፏቴው አስደናቂ ዕይታን ይላበሳል። በፏፏቴው ዙሪያ የሚበሩት ግዙፍ ላመርጊዬር አሞራ እና ሌሎች ብርቅዬ አዕዋፋት ተጨማሪ ውበትን ያላብሱታል።
ከፏፏቴው ፊት ለፊት ምቹ እና ደልዳላ ቦታ አለ። ጎብኝዎች ከዚህ ቦታ ኾነው የፏፏቴውን ሙሉ ገጽታ አሻግረው እንዲያዩት ያስችላቸዋል። ጎብኝዎች ብዙ ጊዜያቸውን ከሚያሳልፉባቸው ቦታዎችም መካከል ነው።
ጎብኝዎች የፏፏቴው ሙሉ ገጽታ ወደሚታይበት ወደዚህ ደልዳላ ቦታ ለማለፍ ታዲያ አንድ ፈተና ያጋጥማቸዋል። እሱም አስደናቂውን የተነባበረ የድንጋይ ድልድይ ማለፍ ነው። በእሳተ ገሞራ እንደተፈጠረ የሚነገረው ይህ ንብርብር ድንጋይ በፓርኩ ውስጥ ረጅም ርቀትን ይሸፍናል።
ንብርብር ድንጋዩ ከፏፏቴው ፊት ለፊት ሲደርስ የፏፏቴውን ሙሉ ገጽታ ለማየት ወደሚያስችለው ደልዳላ ቦታ ለመሸጋገር እንደ ድልድይ ኾኖ ያገለግላል። መሸጋገሪያው በጣም ጠባብ እና በግራ እና በቀኝ ገደል በመኾኑም ለመሻገር ድፍረት ይጠይቃል። ይህን ቦታ የውጭ ጎብኝዎች እንደ ጀብድ ቱሪዝም ይቆጥሩታል። ወደ ፏፏቴው ከመድረሳቸው በፊትም አስደናቂ የጉዞ ማስታወሻ ፎቶዎችን የሚይዙበት ተወዳጅ ስፍራም ነው።
ይህ ንብርብር ድንጋይ የተፈጠረው ከበርካታ ዓመታት በፊት በፈነዳ እሳተ ገሞራ የቀለጠ ድንጋይ ቀስ በቀስ በመቀዝቀዙ እንደኾነ ይነገራል።
ንብርብር ድንጋዮቹ እንደ ሕንጻ ግድግዳ ተሰድረው ሲታዩ በአናፂ የተሠሩ እንጅ ተፈጥሯዊ ሥሪት አይመስሉም። ወደዚህ ቦታ ያቀኑ የውጭ ጎብኝዎች ሁሉ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብታምነት ለመመስከር ሲገደዱ ታይተዋል።
ከሰኔ ወር እስከ መስከረም የውኃው መጠኑ ስለሚጨምር እና ከጥቅምት ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ደግሞ አካባቢው በአረንጓዴ እና በተለያዩ አበባዎች ስለሚዋብ ፏፏቴውን ለጉብኝት ተመራጭ ያደርገዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









