ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መሪዎች በክብር ተጎናጽፈውበታል፤ የሥልጣን ዙፋናቸውን ግርማ ሞገስ ደርበውበታል፤ ክብር እና ዝና የሚገባቸው መልካም ሰዎችም ምሥጋናን ተችረውበታል።
የሃይማኖት አባቶች፣ በወግ በማዕረግ የተዳሩ ሙሽሮች እና ሌሎችም ለክብር ሲባል የሚደምቁበት የክብር ልብስ ነው ካባ።
ለመኾኑ ካባ ምንድን ነው ?
ኃይለ ማርያም ኤፍሬም ድብ አንበሳ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ቅርስ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ በሚል ርዕስ በ2013 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ስለካባ በሰፊው አትተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የክብር ልብስ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ካባ ግንባር ቀደሙ ነው ይላሉ። ካባ እንዲሁ ብቻ የሚለበስ የልብስ አይነት አይደለም ነው የሚሉት።
የቀደምት ነገሥታት የዘውድ ሥርዓታቸውን ሲያከናውኑም ኾነ የተለየ ክብረ በዓል ሲኖር ካባ ደርበው እና በግርማ ሞገስ ተጎናጽፈው እንደነበር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ያን ማድረጋቸውም በክብር ላይ ክብርን ይጎናጸፋሉ ነው ያሉት። የሕዝብ ተቀባይነታቸውንም የበለጠ ከፍ ያደርግላቸዋል ብለዋል።
ካባ በቤተ ክህነትም ኮነ በቤተ መንግሥት ዘንድ የክብር ልብስ ነው፤ የልብሱ አይነት ግን ይለያያል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያን ይመሩ የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ካባ ልዩ መገለጫቸው እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል ብለዋል።
በነገሥታት ዘንድ ዘውድ፣ ልዑል፣ በትረ መንግሥት እና ዙፋን እንዳለ ሁሉ ካባም የኢትዮጵያውያን ነገሥታት የክብር ልብስ ኾኖ የኖረ እንደኾነ ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ነገሥታት ካባን አጊጠውበት፣ ክብራቸውንም ገልጠውበታል።
ነገሥታት ፣ መኳንንት፣ መሳፍንት ካባን ተውበውበታል፤ አጊጠውበታል ብለዋል ደራሲ ኃይለ ማርያም። አሁንም ድረስ በመላው ኢትዮጵያ ካባ አገልግሎት ላይ እየዋለ እንዳለም አንስተዋል።
ከነገሥታት ባለፈም ታላላቅ ሰዎች ግርማ ሞገስን ሲጎናጸፉበት ማየት የተለመደ ነው ብለዋል።
ካባ ላንቃ፣ ልሙጥ ካባ፣ የወርቅ ካባ፣ አጥላስ ካባ እና ሌሎች የካባ አይነቶች አሉ። እንደየ ማዕረግ እና እንደየ ደረጃው ትርጉም በሚሰጥ መንገድ እንደሚጌጥም አንስተዋል።
ድርቧ ደበበ (ዶ.ር) በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህርት ናቸው። ባሕል የአንድን ማኅበረሰብ ወጉን፣ ልማዱን፣ አኗኗሩን እና አጠቃላይ የሕይወቱን ገጽታ የሚያጠቃልል ሰፊ ነገር ነው ብለዋል። ባሕል እንደ ውቅያኖስ ሁሉ ጥልቅ ነው፤ የሰው ልጅ በምድር ላይ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሚገነባው በባሕል ነው ይላሉ።
ከዚያ ጥልቅ የባሕል ውቅያኖስ ውስጥ የአለባበስ ባሕሉ አንድ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል። አልባሳት በፎክሎር ጥናት ውስጥ ከቁሳዊ ባሕል የሚመደብ እንደኾነ ተናግረዋል። ሀገረሰባዊ የእጅ ጥበብ ሥራ እንደኮነም ገልጸዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ብዙ ነገር ቢያመሳስላቸው እንኳ ማንነታቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ሌሎችን ነገሮች ምክንያት አድርጎ አለባበስ አንዱን ከአንዱ ይለያያል፤ ይህም አለባበሳችን የአንድ ማኅበረሠብ መለያ ነው ብለዋል።
አልባሳት በአንድ ዘመን ላይ የነበረን ማኅበረሰብ ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያሉ ነው ያሉት።
ካባ መልበስ ትናንትም የነበረ ባሕላችን ስለኾነ ባሕሉን ማስቀጠል እና አለባበሳችን ከራሳችን ባሕል እና ወግ እንዳይወጣ መሥራት አለብን ብለዋል። ምክንያቱም የሰው ወርቅ አያደምቅ ነውና ነገሩ ይላሉ።
#አሚኮ_ዜና #ባሕል_አልባሳት_ካባ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









