‎ማይስ ቱሪዝም በኢትዮጵያ ‎

0
79

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ የመስህብ ሃብቶች ባለቤት ናት። እነዚህን የመስህብ ሃብቶች በመጠበቅ እና አልምቶ ለመጠቀም እንዲቻል ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኾኖ እየተሠራበት ይገኛል።

‎ቱሪዝም ከጉብኝት ዓላማ አንጻር የተለያዩ አይነቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል ማይስ (MICE) ቱሪዝም አንዱ ነው፡፡ ማይስ ቱሪዝም ስብሰባዎችን እና ኮንፈረንሶችን መሠረት ያደረገ የቱሪዝም አይነት ነው፡፡

‎ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ስብሰባዎችን እና ኮንፈረንሶችን ታስተናግዳለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2027 የሚካሄደውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔን (COP 32) በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ የጉባዔው አባል ሀገራት መስማማታቸው ተነግሯል፡፡

‎ለመኾኑ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ለሀገሪቱ ቱሪዝም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

‎በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኀላፊ የሽዋስ አቡኔ (ዶ.ር) ቱሪዝም በተለያዩ የኩነት አይነቶች የሚተገበር ሲኾን ማይስ (MICE) ቱሪዝም ደግሞ አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡

በውስጡም ስብሰባን፣ የማበረታቻ ጉዞ (ኢንሰንቲቭ)፣ ኮንፈረንስን እና ኤግዚቪሽንን የያዘ ስለመኾኑ ገልጸዋል፡፡

‎ማይስ ቱሪዝም የተለያዩ ሰዎችን ሥርዓት ፈጥሮ እንዲሰባሰቡ በማድረግ የሚተገበር የቱሪዝም ዘርፍ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶችን አንስተዋል፡፡

‎ኢትዮጵያ እንደ (COP 32)፣ የኢጋድ እና አፍሪካ ኅብረት አይነት ዓለም አቀፍ እና አኅጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማዘጋጀት ዕድል መገኘት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዓለም አቀፍ በኾነ ሁኔታ ለማስተሳሰር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

‎የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ሀገራትን እና አሕጉራትን የሚወክሉ ግለሰቦች ውይይት ለማድረግ ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

‎ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ያስችላል ነው ያሉት። ለዚህም በመንግሥት በዕቅድ ተይዞ ከኮንፈረንሱ እኩል ታስቦበት መተግበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

‎ዓለም አቀፍ ግንዛቤ እና አረዳድ ያላቸው ሰዎችን በቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

‎በሀገሪቱ በቱሪዝም መስክ የተሰማሩ የሆቴል ባለሃብቶች፣ አስጎብኝዎች እና የጉዞ ወኪሎች የገቢ ምንጫቸው እንዲጨምር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲኖራቸው የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

‎የግለሰቦች የገቢ ምንጭ ሲጨምር ሀገራዊ የሀገር ውስጥ ጥቅል እድገት ያድጋል፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የሚያንቀሳቅሰው ሞተር ጥሩ የኢኮኖሚ ገጽታን የመፍጠር አቅም ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

‎ቱሪዝም ትልቅ የሀገር ገጽታን የመቀየር አቅም ያለው የኢንዱስትሪ ሴክተር ነው ብለዋል፡፡ የቱሪዝም ቢዝነስ የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎችን ያንቀሳቅሳል፣ ኢኮኖሚውንም ያሳድጋል።

‎ጎብኝዎች ሲጨምሩ አስጎብኝዎች፣ የጉዞ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት፣ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት የሚሳተፉ ሁሉ ተጠቃሚነታቸው ይጨምራል ብለዋል፡፡

‎ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ እንዲነቃቃ እና ለቱሪዝም ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር ስለሚያደርግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቱሪዝም ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

‎ኮንፈረንስ ትልቅ የቱሪዝም ማንቀሳቀሻ መንገድ ወይም እይታ በመኾኑ እጅግ አስፈላጊ ከኾኑት የቱሪዝም የማስፈጸሚያ ስልቶች አንዱ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

በተለይም አሁን ካለው የከተሞች እድገት ጋር ኮንፈረንስ ቱሪዝም ወደፊት የመተግበር ዕድሉም ሰፊ ነው ተብሎ ይገመታል ነው ያሉት፡፡

‎የቱሪዝም ሴክተር በባህሪው መሠረተ ልማትን ማሳደግ እና ሰላምን የሚፈልግ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ የሚጎበኙ መዳረሻ ቦታዎችን ለማስጎብኘት ማልማት እና ከለሙ በኋላ ማስጎብኘት የሚችል ባለሙያ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

‎እንደዚህ ሁሉ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚፈልጋቸው አገልግሎቶች አሉ፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ የሆቴል አገልግሎቶች እና የመሰብሰቢያ አዳራሾች እንዲሁም ጥሩ የአገልግሎት አሰጣጥ መኖር እንዳለበትም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

‎አሁን ለተገኘው አይነት የኮንፈረንስ ዕድሎችም ቀደም ብሎ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here