ባሕር ዳር: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለባሕር ዳር ልዩ ገጸ በረከት የኾነው የጣና ሐይቅ በሰማያዊ ድምቀቱ ከከተማዋ ጋር ተዋሕዶ ይታያል። ምሽት ላይ በሐይቁ ዳርቻ የሚኖረው የቀዝቃዛ አየር እና የፀሐይ ግባት ውበት በቃላት የማይገለጽ ሰላምን ይፈጥራል፤ ሀሴትን ያጎናጽፉል።
በሐይቁ ላይ የሚታዩት ታሪካዊ ገዳማት እና ደሴቶች ለባሕር ዳር መንፈሳዊ እሴትን ጨምረውላታል። በከተማዋ ሰፋፊ መንገዶች ዳርቻ የተተከሉ ዘንባባዎች መንገደኛውን ሁሉ በጥላነታቸው ቤተኛ ያደርጉታል።
በከተማዋ የተሠሩት የኮሪደር ልማ ሥራዎችም ተደብቆ የኖረውን የጣናን ውበት ገልጠውታል። የከተማዋ መንገዶች ተውበዋል። ባሕር ዳር በየጊዜው በውበት ላይ ውበት፣ በድምቀት ላይ ድምቀት እየጨመረች በዓባይ ወንዝ ላይ ነግሳለች።
ብዙዎች ፈጣሪ ለባሕር ዳር አዳልቷል በማለት አድናቆታቸውን ይገልጻሉ። የውጭ ሀገር ዜጎች እና ዲፕሎማቶችም ስለውበቷ እና ስለ ምቾቷ ይናገራሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕርግራም የሰላም ድጋፍ ማዕከል በኢትዮጵያ አሥተባባሪ ሞንትሶፍ ካተርስ በየወቅቱ ወደ አማራ ክልል ባሕር ዳር እንደሚመላለሱ ነግረውናል።
ባሕር ዳር ከተማ ውብ እና ድንቅ እየኾነች መምጣቷንም ይገልጻሉ። ውጤታማ የኾኑ ልማቶችን እያከናወነች እንደምትገኝ ተመልክቻለሁ ነው ያሉት። ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከተማ እየኾነች መምጣቷንም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ክፍል አርክቴክቸራል ሴክሬታሪያት የኾኑት ሳላህ አሕመድ ውብ የኾነችዋን ባሕር ዳርን በመጎብኘቴ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ባሕር ዳር በጣና ዳርቻ እና በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገኝ ማራኪ ገጽታ ያላት ምቹ ከተማ ስለመኾኗ ተናግረዋል ። ከተማዋን ከረጅም ጊዜ በፊት አውቃታለሁ፤ አሁን ላይ ግን ብዙ ለውጦችን አይቻለሁ፤ ብዙ የቱሪስት መስህቦችም ለምተዋል ነው ያሉት።
ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትኾን ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም መዳረሻ ናት ብለዋል። በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ይህችን ውብ ከተማ እንዲጎበኟት እና ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ እጋብዛቸዋለሁ ብለዋል።
ዘጋቢ :- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









