የአባት ውርሱ – ደንቀዝ ቤተ መንግሥት !

0
67

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚገኙ ቀደምት ቅርሶች መካከል ደንቀዝ ቤተ መንግሥት አንዱ ነው።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከማክሰኝት ከተማ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ቤተ መንግሥቱ እና በአቅራቢያው ያለው ሕንጻ የቀደምት አባቶች እጅ ያረፈባቸው ለየት ያለ የአሠራር ጥበብ ያላቸው ናቸው።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ጌታሰው ታደለ ደንቀዝ ቤተ መንግሥት እና በቅርቡ የሚገኘው የንጉሱ ቀኝ እጅ የነበሩት የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ትምህርታዊ አገልግሎት መስጫ የነበረ ሕንጻ በአጼ ሱስንዮስ አማካኝነት በ1920ዎቹ ዓ.ም እንደተገነባ ነግረውናል።

ለቤተ መንግሥትነት ያስገነቡት ሕንጻ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ፎቅ እንደኾነ ነው የጠቀሱት። የውስጠኛው ክፍል ግርግዳ አሁንም የሚታዩ ጥንታዊ ስዕሎች ያሉበት ነው ብለውናል።

ከዚህ ባሻገር በወቅቱ ለውኃ ማጠራቀሚያ ያገለግል የነበረ እና ክዳን እና ወደታች መውረጃ እና መውጫ ያለው ከምድር ቤቱ ታች ጥልቀት ያለው ትልቅ የውኃ ገንዳ አለው ነው ያሉት።

የአጼ ሱስንዮስ ጌጣጌጥ እና ገንዘብ ማስቀመጫ ኾኖ ያገለግል የነበረ ከግድግዳው ጋር የተያያዘ በኖራ የተሠራ ካዝና መኖሩንም ተናግረዋል።

ንጉሡ በቤተ መንግሥታቸው ግብዣ በሚያደርጉ ጊዜ ማኅበረሰቡ ከቤተ መንግሥቱ ግቢ ኾኖ ሲጋበዝ ከውስጠኛው ክፍል ወደ ውጭ ጠጅ የሚተላለፍበት በኖራ የተሠራ ወደ ማጠራቀሚያ ጋን ጠጅ የሚያስተላለፍ መውረጃ መኖሩንም ጠቅሰዋል። አሁንም ድረስ ሳይፈራርስ ይገኛል ብለዋል።

ሁለተኛው ሕንጻ ደግሞ ከላይ ሲታይ የመስቀል ቅርጽ ያለው ለካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ትምህርታዊ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ እንደኾነ ገልጸውልናል። ይህ ሕንጻ የውስጥ እና የውጭ ግድግዳዎቹ በተወሰነ ደረጃ የተጎዱ ቢኾንም በውስጥ የተሠሩለት ጌጣጌጥ እና ቅርፃ ቅርፆች ዛሬም ድረስ ጎልተው እንደሚታዩ ነግረውናል።

አሁን ላይ ቅርሱ በዕድሜ ብዛት እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰበት እንደኾነም አንስተዋል። ቀደም ሲል ቤተ መንግሥቱን ከማጽዳት እና በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ከማስተዋወቅ ባሻገር ጥገና እና እንክብካቤ እንዳልተደረገለት ተናግረዋል።

ቅርሱን ከጉዳት ለመታደግ እና ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገርም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ እና አጋር አካላትን እገዛ ጠይቀዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ከተማ ነዋሪው ግርማቸው ሙሉጌታ የደንቀዝ ቤተ መንግሥትን የአካባቢው ማኅበረሰብ በኩራት የአባት ውርስ አድርጎ በባለቤትነት እንደሚመለከተው ነግረውናል። አሁን ላይ ግን በተለያየ ምክንያት የመፈራረስ አደጋ እንደገጠመው ነው የነገሩን።

የመንገድ መሠረተ ልማት በተገቢው ሁኔታ እንዳልተሠራለትም አንስተዋል። የመብራት ችግር እና ቅርሱ የሚገኝበት ዙሪያ የአርሶ አደሮች የእርሻ መሬት በመኾኑ ቅርሱ በተገቢው ሁኔታ የቱሪስት መዳረሻ እንዳይኾን ማድረጉንም ተናግረዋል።

ደንቀዝ ቤተ መንግሥት እና አካባቢው ብዙ ቅርሶች የሚገኙበት በመኾኑ ቅርሱ ቢለማ እና ቢጠገን የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚኾንም ገልጸውልናል። ለዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያየ ጊዜ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ እያቀረበ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ኑርሁሴን ሁሴን የደንቀዝ ቤተ መንግሥት ጥገና እና እንክብካቤ እንዲደረግለት ከወረዳ እስከ ክልል ካሉ የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መዋቅሮች ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የቅርሱ ዙሪያ ከሦሥተኛ ወገን ነጻ ይሁን የሚል ሀሳብ ግን ከዚህ በፊት እንዳልቀረበላቸው ነው የገለጹት።

በቅርሱ ዙሪያ ያሉ የእርሻ መሬቶች የቅርሱ ደኅንነት ላይ የሚፈጥሩት ጫና ካለ በቀጣይ በጥናት ተለይቶ የመሬት አዋጁ በሚፈቅደው መሠረት አርሶ አደሮች የይዞታ መብታቸው ተጠብቆ ተገቢውን ካሳ አሊያም ትክ መሬት በመስጠት የቅርሱን ደኅንነት ለመጠበቅ እንሠራለን ብለዋል።

በቅርቡም ወደ ሥራ እንገባለን ነው ያሉት።

በሮዛ የሻነህ

#አሚኮ_ዜና #ቱሪዝም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here