ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቦታው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ነው፤ ታሪካዊው ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም።
በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተመሠረተው ታሪካዊው ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ውስጥ ታዲያ “የሥላሴ ከብቶች” የሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የከብት መንጋዎች ይገኛሉ።
እነዚህ ከብቶች ከተለመደው የእንስሳት ባህሪ ውጭ በኾነ ረቂቅ ሥርዓት እና ፍቅር ይመራሉ።
የገዳሙ አፈ-መምህር አባ አማሃ ኢየሱስ ወልደ ሥላሴ እንደሚያብራሩት በእነዚህ እንስሳት እና በሰዎች መካከል አስገራሚ ተግባቦት አለ ይላሉ።
“ላምራስ” በመባል የሚታወቁት የገዳሙ መነኮሳት ከብቶቹን የሚመሩት በዱላ ሳይኾን በለስላሳ ቃል እና የፍቅር ቃና ነው።
እረኛው “ተመለስ” ወይም “ቁም” ሲላቸው ወዲያውኑ ይታዘዛሉ። ጥጃዎችን ከእናቶቻቸው ለይቶ ወደ ግጦሽ ለመውሰድ ሲፈለግም ላምራሱ “ወገን” እያለ ሦሥት ጊዜ ሲያጨበጭብ ጥጃዎቹ ያለምንም ግርግር ተለይተው በሰልፍ ይጓዛሉ።
በሺዎች በሚቆጠሩ መንጋዎች መካከል እያንዳንዱ ላም እና ጥጃ የሰው ጆሮ የማይለየው ልዩ የድምጽ ቃና አላቸው። ጥጃዎቹ ወተት ጠብተው ሲጨርሱ እረኛው “አጎዶ” (ማደሪያ በረት) እያለ ሦሥት ጊዜ ሲያጨበጭብ የራሳቸውን ማደሪያ አውቀው በፈቃዳቸው ይገባሉ።
መንጋውን ወደ ሌላ የግጦሽ ቦታ ለማዛወር ላምራሱ “ጉዞ” እያለ ሦሥት ጊዜ ሲያጨበጭብ ጉዟቸውን ይጀምራሉ። መድረሻቸው ላይ ሲደርሱም “ሠፈር” በሚል የሦሥት ጊዜ ጭብጨባ በአንድነት ይቆማሉ።
በተጨማሪም በገዳሙ የጸሎት እና የቅዳሴ ደወል ሲሰማ በእንስሳቱ ላይ ልዩ ጸጥታ ይሰፍናል።
“ሰው እግዚአብሔርን ሲታዘዝ፣ ፍጥረት ሁሉ ደግሞ ሰውን ይታዘዛል፤ የገዳሙ ሕግ እና ሥርዓት በእኛ ላይ ብቻ ሳይኾን በእነሱም ላይ ይሠራል” ይላሉ አባ አማሃ ኢየሱስ።
የማኅበረ ሥላሴ ከብቶች ታሪክ፣ ፍጥረት ሁሉ በፈጣሪ እና በሰው ልጅ ፍቅር ሲገራ ምን ያህል ውብ እና ሰላማዊ ሥርዓት ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ ድንቅ የሕይወት ትምህርት ነው።
#አሚኮ_ዜና #ልዩ_እንሰሳት #ምዕራብ_ጎንደር #መተማ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !









