ልክ እንደ ዋሊያ ሁሉ ከኢትዮጵያ ብርቅዬ አጥቢ እንስሳቶች አንዱ የኾነው ጭላዳ ዝንጀሮ በስሜን ተራራዎች ላይ ከትሞ ይገኛል። አልፎ አልፎም በሌሎች የሀገሪቱ ተራራማ አካባቢዎች ይስተዋላል።
ለየት ባለ እና ውብ በኾነው ቀይ ቡናማ ፀጉሩ ምክንያት “የዝንጀሮ አንበሳ” (lion monkey) የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ጭላዳ በሌሎች የአፍሪካ አካባቢዎች ከሚገኙት ተራ ዝንጀሮዎች ፈጽሞ የተለየ፣ ጨዋ እና ጠንቃቃ ፍጡር ነው። በወንዶቹም ኾነ በሴቶቹ ደረት ላይ የሚታየው የልብ ቅርጽ ያለው ቀላ ያለ ቆዳ ለዚህ ዝርያ “የሚደማ ልብ ያለው ዝንጀሮ” (bleeding-heart baboon) የሚል ሌላ ቅጽል ስም እንዲሰጠው ምክንያት ኾኗል።
ጭላዳዎች እፅዋት ተመጋቢዎች ሲኾኑ በሰሜን ተራራዎች አረንጓዴ ቁልቁለቶች ላይ የሚመገቡትን ስር እና አምፖል መሰል እፅዋት እየቆፈሩ እና እየተመገቡ በብዙ መንጋዎች ኾነው ሲዘዋወሩ ይታያሉ።
ማኅበራዊ ልማዳቸው በትብብር ላይ የተመሠረተ እርስ በርስ በመጎራረስ ፍቅራቸውን የሚገልጹ እና የፀጉራቸውን ንጽሕና ከተባዮች ለመጠበቅ የሚተባበሩ ናቸው።
አብዛኛውን ጊዜ ለሴት ጭላዳ በሚደረግ ፉክክር ምክንያት በወጣት ወንድ ጭላዳዎች መካከል ጠብ ይነሳል፤ ከዛም የጥንቃቄ እና የቁጣ ጩኸት ያሰማሉ።
ጭላዳዎች መኖሪያቸውን ከሚጋሩት ዋሊያዎች ጋር በተመሳሳይ መልኩ ዓይናፋር ፍጥረታት በመኾናቸው በድብቅ ከተከታተሏቸው ይሸሻሉ፤ በገደል ዳርቻዎች ላይ በመዝለል ከሥር ወደሚገኙት ራቅ ያሉ ሸንተረሮች እና ወጣ ገባ ድንጋዮች ውስጥ በመግባት እንደሚሰወሩ አንደር ኢትዮጵያን ስካይስ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዘመኑ መኮነን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









