🤝ዘመን ተሻጋሪው የጋራ መረዳዳት እሴት ደቦ

0
65

​
በዘመናዊነት ማዕበል ውስጥም ቢኾን የኢትዮጵያ ሕዝብ የቆየ ማኅበራዊ እሴቶች እና የጋራ መረዳዳት ባሕሎች አሁንም ድረስ ተጠናክረው ቀጥለዋል። ከእነዚህም መካከል ደቦ፣ ወንፈል፣ ጂጊ እና ወበራ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ባሕላዊ የሥራ ማሳለጫዎች ተግባራቸው አንድ ቢኾንም እንደየ አካባቢያቸው መጠሪያቸው ይለያያል።

​የወንፈል እና የደቦ ሥርዓት ከዕለት ተዕለት የኑሮ ማቅለያነት ባለፈ፣ የአካባቢን ማኅበራዊ ትስስር አጠናክረው የሚያስቀጥሉ ትልቅ ባሕላዊ ክዋኔዎች ናቸው። በተለይም ከዕለት ተዕለት የእርሻ ሥራዎች ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ሠርግ እና የሀዘን ሥርዓቶች ድረስ አብሮ የመቆም፣ የመደጋገፍ እና የመተሳሰብ እሴት ይታይባቸዋል።

በወንበርማ ወረዳ የማርቁማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላ አረጋ በግብርና ሥራቸው ሂደት ባሕላዊ የኾኑ ማኅበራዊ መሥተጋብሮችን በመጠቀም ሥራቸውን እያቀላጠፉ እንደሚገኙ ነግረውናል።

​አርሶ አደሩ እንደሚሉት ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ አባላት በደቦ ወይም በወንፈል ተሠባሥበው “ዛሬ ለአንዱ ነገ ደግሞ ለሌላው” እያሉ ሥራዎችን በቅንጅት ያከናውናሉ።

ይህ የትብብር ስልት ከእርሻ ጀምሮ እስከ ምርት መሠብሥብ ሂደት ድረስ በስፋት ይሠራበታል ነው ያሉት። የኅብረቱ አባላት ተራ በተራ በሚሠሩበት ጊዜ ምግብ ከየቤቱ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ቦታው ይወሰዳል።

የጋራ ሥራው አላስፈላጊ የጉልበት ሠራተኛ ወጭን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።ጊዜን በመቆጠብ ሥራን አቀላጥፎ በወቅቱ እና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት። ማኅበራዊ ትስስርንም በማጠናከር በቤተሰባዊነት መንፈስ እርስ በርስ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ጠንካራ ማኅበራዊ ቁርኝት ይገነባል ይላሉ።

የአማራ ክልል የባሕል፣ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ በ2001 ዓ.ም ባሳተመው “የአማራ ሕዝብ ባሕል እና ቋንቋ” መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው
በክልሉ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የተጻፈ ደንብ እና መመሪያ ሳይኖራቸው በጋራ ስምምነት እና መረዳዳት ላይ በመመሥረት ከሚዘውሯቸው እጅግ ጠቃሚ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተቋማት መካከል ደቦ እና ወንፈል እንደሚገኙበት ያብራራል።
​
ወንፈል ወይም ደቦ ሀገር በቀል እና ነባር የኅብረት ሥራ ማኅበር ኾኖ ዝምድና፣ ቀረቤታ እና ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ትልቅ ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ለአንድ የማኅበረሰብ አባል በጋራ የሚያከናውኑበት እንደኾነም በመጽሐፉ ተከትቦ ይገኛል።

ደቦ ሰዎች ወረፋ በመግባት ቅደም ተከተልን ጠብቀው ለአንድ የቡድኑ አባል ጥቅም የጉልበት ሥራ የሚሠሩበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

በተለይም እጅግ አድካሚ እና አሰልቺ የኾኑ የግብርና ሥራዎችን በመተባበር እና በመተጋገዝ ለማከናወን እንደሚያገለግል ያትታል። በርካታ የሰው ኀይል በሚፈልጉ እንደ እርሻ፣ አጨዳ እና አረም ባሉ ተግባራት ላይ የተወሰነ ቡድን ተቋቁሞ በወረፋ የሚሠራበት እንደኾነም በግልጽ ተቀምጧል።

ይህ የማኅበራዊ ጉልበት እና የአገልግሎት ልውውጥ ሥርዓት ለሁለቱም ጾታዎች ያገለግላል። ወንዶች ብዛት ባላቸው ጥንድ በሬዎች መሬት ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ቤት ለመሥራት፣ አጥር ለማጠር እና ሰብል ለማረም እርስ በእርስ ይጠቃቀማሉ። ሴቶች ደግሞ ጥጥ ለመፍተል፣ ቤት ሢሠራ ውኃ ለመቅዳት፣ የሰንበቴ ማኅበር እና የሠርግ ድግስ ለመደገስ ማኅበራቱን አቋቁመው በኅብረት እንደሚሠሩበት በመጽሐፉ ተገልፆ ይገኛል።

​ወንፈል ወይም ደቦ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር የላቀ ማኅበራዊ ፋይዳ አላቸው። ሰዎች ዕምነታቸው፣ ቋንቋቸው፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ደረጃቸው ሳይገድባቸው በመረዳዳት የሚጠቀሙባቸው ውብ ነባር ሀገር በቀል የኅብረት ሥራ ማኅበራት መኾናቸውን በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል።

ይህ አሠራር ማኅበረሰቡ ሀገር በቀል ዕውቀትን በመጠቀም የግብርና ሥራዎችን ከማቀላጠፍ ባለፈ አንዱ ለሌላው መረዳዳት እና አብሮነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይበት አርዓያነት ያለው ተግባር ነው።

#አሚኮ #ባሕል_ #እሴት #TraditionalCooperation

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here