🌃 ከባሕር ዳር ከተማ በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዳጋ እስጢፋኖስ፣ ናርጋ ስላሴ፣ ቅድስት አርሴማ፣ ኮታ ማርያም፣ ዝባድ ኢየሱስ፣ ጆጋ ዮሐንስ እና ጋደና ጊዮርጊስ በደሴቱ ውስጥ የሚገኙ ገዳማት ናቸው፡፡
🌊 የጣና ሐይቅ በውስጡ ከያዛቸው ዕንቁ ደሴቶች መካከል በአቀማመጡ እና በስፋቱ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል ደቅ ደሴት። በውኃ የተከበበው ደቅ ደሴት ነፋሻማ አየሩ መንፈስን ያድሳል፤ ሀሳብ እና ጭንቀትን ያርቃል፤ ለዓይን የሚማርከው ተፈጥሯዊ አቀማመጡ ደስታን ይፈጥራል።
ወደ ደቅ ደሴት ለመጓዝ ከጣና ሐይቅ የሚነሳውን ነፋሻማ አየር እየማጉ፤ የሐይቁን የውኃ ጨዋታ እየተመለከቱ፤ በሐይቁ መካከል የሚገኙ ደሴቶችን በርቀት እያስተዋሉ ለሰዓታት የሚፈጅ የጀልባ 🚣♀️ ጉዞን መጠቀም ግድ ይላል።
በጣና ሐይቅ ደቅ ደሴት ላይ ተወልዶ ያደገው ዮሴፍ ሽፈራው ደቅ ደሴት “ሕጻን ልጅ ወይንም ትንሽ” የሚል ትርጓሜ በማኅበረሰቡ እንደተሰጠው ይናገራል። በውስጡ ሰባት አድባራት መኖራቸውንም አጫውቶናል።
የአቡነ ሂሩት አምላክ፣ የአጼ በካፋ፣ የአጼ ሱስንዮስ አጽም የሚገኝበት ዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ሌሎች ገዳማት እንዳሉም ተናግሯል። የደሴቷን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እና ማልማት ከተቻለ የቱሪዝም መዳረሻ በመኾን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻልም ነው የተናገረው።
የደሴቱ ኅብረተሰብ መገዳደልን የሚጸየፉ፤ ችግሮችን በውይይት እና በሽምግልና ሥርዓት መፍታትን 🤝 ባሕል አድርገው እንደሚኖሩም ገልጿል።
በደሴቱ ሁለት የአንደኛ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ደሴቱ በውኃ የተከበበ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ወደ ባሕር ዳር፤ ጎንደር እና ሌሎች አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ጀልባዎችን 🛥 መጠቀም ብቸኛ አማራጭ መኾኑን ነው ያነሳው። ደሴቱ በውኃ የተከበበ በመኾኑ ለዓሳ ምርት ምቹ መኾኑንም ተናግሯል።
ሌላኛው የደሴቷ ነዋሪ ያደለው ረዳት ማኅበረሰቡ በእርሻ ልማት በቆሎ፣ ፈንድሻ፣ በርበሬ እና ዳጉሳን በይበልጥ ያመርታሉ ይላል። ማንጎ እና ሙዝ ደግሞ በቋሚ ተክል በስፋት በማምረት የምግብ ፍጆታቸውን እንደሚሸፍኑም ተናግሯል።
የፈንድሻ እና የማንጎ ምርትን በይበልጥ ማልማት ከተቻለ እና የገበያ ትስስር ከተፈጠረ ማኅበረሰቡ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚኾንም አጫውቶናል።
ደቅ ደሴት በሐይቅ ብትከበብም ለእኛ እንደ የብስ ነች ያለው ነዋሪው ደቅ ደሴትን እንደ ጎርጎራ ማልማት ከተቻለ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መኾን እንደምትችልም አመላክቷል።
#አሚኮ #ደቅ_ደሴት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









