ተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ውበት የተዋሃዱባት፣ ሳይንሳዊ ምስጢር እና ጥንታዊ ሥነ ቃሎች የተገናኙባት ባሕር ዳር

0
38
 
ውኃ በውኃ ላይ ተለይቶ ሲጓዝ ማየት ከተፈጥሮ ሕግ የወጣ ትዕይንት ይመስላል። ነገር ግን የዐይን ምስክርነት ያለው ድንቅ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ይህ ሕግም ጣና ሐይቅ ላይ የታተመ ይመስላል። ለባሕር ዳር ደግሞ ሌላ በረከት ኾኗል። የዓባይ ውኃ በጣና ውኃ ላይ ሲጓዝ የሚታይበት ልዩ ትዕይንት ነው። ከዚህ በመነሳትም የአካባቢው ማኅበረሰብ “ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት፣ ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት” እያለ
በዜማ የተፈጥሮን ድንቅ ጥበብ ሲገልጽ ኖሯል። ይህ ጥንታዊ እና ውብ ሕዝባዊ ሥነ ቃል ትውልድ ተሻግሮ ዛሬም በሰዎች አንደበት ይነገራል። ባሕር ዳር ተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ውበት ተዋህደውባታል። ሳይንሳዊ ምስጢር እና ጥንታዊ ሥነ ቃልም ተገናኝተውባታል። ዓባይ እና ጣናም ላይለያዩ ቃል ኪዳን የገቡ ይመስል ተዛምደውባታል። ለሀገር ውስጥም ኾነ ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች ድንቅ መዳረሻነቷንም እያረጋገጠች ነው።
ውኃ በውኃ ላይ ሰለመሄድ ሳይንስ ምን ይላል? ወንዞች ወደ ሐይቅ በሚገቡበት እና በሚወጡበት ሥፍራ ላይ የሚፈጠረውን ፍሰት የሚያጠኑ የፈሳሽ እንቅስቅሴ ሳይንስ (hydro dynamics) እና የውኃ ሳይንስ (hydrology) ዘርፎች ውኃ በውኃ ላይ የመሄድ የተፈጥሮ ክስተት እንዳለ በግልጽ ያረጋግጣሉ። ይህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ዓባይ ጣናን አቋርጦት ይሄዳል ለሚለው በሥነ ቃል የተደገፈ እና በዐይን የሚታይ
ትይንት ሳይንሳዊ መሠረት ይሰጣል።  ሥፍራውን ለቱሪዝም ለመጠቀም ምን ተሠራ? የባሕር ዳር ከተማን ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት ተንተርሶ ጣና አካባቢ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ዓባይ በጣና ላይ የሚጓዝበትን ትይንት በቅርብ ኾኖ ለመመልከት ዕድል ፈጥሯል። በተለያዩ
ጊዜያት በባሕር ዳር ከተማ የተከናወነው ሰፊ የከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጄክቶችን አስመልክቶ አሚኮ የሠራቸው ዘገባዎች እንደሚያስረዱትም የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት ከጣና ሐይቅ እና ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ ጋር በማስተሳሰር የቱሪስት ፍሰቱ እንዲነቃቃ ትልቅ አስተዋጽኦ
አድርጓል። ይህም ጎብኝዎች በእግር፣ በብስክሌት እና በጀልባ መዳረሻዎችን በቀላሉ እና በምቾት እንዲጎበኙ አስችሏል። ዓባይ ከጣና በሚወጣበት አካባቢ ዘመናዊ የጀልባ ማቆሚያዎች እና መነሻዎች ተገንብተዋል። ጎብኝዎች በዘመናዊ ጀልባዎች ወይም በጥንታዊው የደንገል (ፓፒረስ) ባሕላዊ ታንኳ በመጠቀም ይህንን መለያያ መስመር በጥልቀት እንዲመለከቱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። የባሕር ዳር ቱሪዝም ማኅበራት መረጃ
እንደሚያመለክተው የተደራጁ የባሕር ዳር አስጎብኝዎች፣ የጀልባ ባለቤቶች እና የትራንስፖርት ማኅበራት ጎብኝዎች ያለምንም እንግልት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ በሠለጠኑ ባለሙያዎች የታገዘ የጉብኝት አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጉ ይገኛሉ። እንደ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋዊ
መረጃዎች ይህ አስደናቂ የተፈጥሮ መዳረሻ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን አዲሱን “የኢኮኖሚ ሞተር” የመገንባት ስትራቴጂ አካል ኾኗል። በወንዙ እና በሐይቁ ዳርቻዎች ላይ ክፍት የአየር አምፊቲያትሮች፣ የመዋኛ ገንዳዎች እና መናፈሻዎች ተገንብተው አካባቢውን የቅርስ፣ የተፈጥሮ እና የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራም ይገኛል።
📍 እርስዎስ ይህን ዓይነት ትይንት አይተው ያውቁ ይኾን? አስተያየትዎን በኮሜንት ያጋሩን👇
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here