🏔️🪨ተፈጥሮ በልዩ ጥበብ የሠራችው ከአንድ ዓለት ድንጋይ የተፈጠረው የተፈጥሮ ድልድይ “በፍታው”

0
44

 

የ”በፍታው” የተፈጥሮ ድልድይ በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰከላ ወረዳ ከሚገኙ ተፈጥሯዊ መሥህቦች መካካል አንዱ ነው።

ይህ ድልድይ ከወረዳው መቀመጫ ከግሽ ዓባይ ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በዓባይ ተፋሰስ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሱርባ ቢፈታ ቀበሌ ይገኛል።

የሰከላ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አማረ መብራቱ በወረዳው በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የመሥህብ ሥፍራዎች ይገኛሉ ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል ከአንድ ዓለት ድንጋይ የተፈጠረው ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊው የ”በፍታው” የተፈጥሮ ድልድይ አንዱ ነው ይላሉ።

ድልድዩ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የተዘረጋ፤ የፋግታ ለኮማን እና የሰከላ ወረዳዎችን ለማገናኘት የተፈጠረ ይመስላል ነው ያሉት።

“በፍታው” የተፈጥሮ ድልድይ በሥተ ምሥራቅ ሠከላ፣ በሥተ በምዕራብ ፈግታ ለኮማን እና በሰሜን ሜጫ ወረዳዎችን የሚያዋስን ነው።

ሦሥቱን ወረዳዎች በማገናኘት ላይ የሚገኝ ድንቅ መሥህብ መኾኑንም ነው ያስረዱት።

​የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በማገናኘት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ይህ ድልድይ በክረምት ወቅት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ትልቅ ችግር እየፈታ ይገኛል ብለዋል።

ድልድዩ የዓባይ፣ የዳቦላ እና የጉግሪ ወንዞች በአንድ ላይ የሚገናኙበት አካባቢ ነው ።

ውኃውም በተፈጥሮ ድልድዩ ሥር አድርጎ ያልፋል። ልዩ ፏፏቴ ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ቦታው በጥንት ጊዜ በተለይም በሥሩ በሚገኘው ተፈጥሯዊ ዋሻ ውስጥ ንዋየ ቅዱሳንን ከጉዳት ለመጠበቅ አባቶች ያስቀምጡበት እንደነበረ ይነገራል ነው ያሉት።

በአካባቢው የተፈጥሮ ዛፎች መኖራቸውንም ያነሳሉ።

ይህ ተዓምራዊ የተፈጥሮ ድልድይ በምቹ የአየር ፀባይ ተከቦ ሲመለከቱት ዕይታን የሚስብ መንፈስን የሚያድስ ድንቅ ተፈጥሮ ነው።

​ይህ ድልድይ ከተፈጥሯዊ ውብ አፈጣጠሩ ባሻገር የሦሥቱን ወረዳዎች ማኅበራዊ ትስስር እያጠናከረ ይገኛል።

ቦታውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የገለጹት ባለሙያው በተለይም የመንገድ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።

#አሚኮ#አማራክልል #ቱሪዝም #የተፈጥሮ ድልድይ# ኢትዮጵያ 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here