ደምጎርሳ ጊዮርጊስ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ይገኛል። ይህ ጥንታዊ ቅርስ ከጥንታዊቷ ደጎማ ከተማ በስተምሥራቅ በኩል አምስት ኪሎ ሜትር፤ ከታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በ41 ኪሎ ሜትር እና ከማክሰኝት ደግሞ በ21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ዘመኑ በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የተጻፈበት 1535 ዓ.ም ነበር። ታላቁ ንጉሥ አጼ ገላውዲዮስ በወይናደጋ ምድር በዘመኑ የነበረ ጦርነትን በድል አድራጊነት የመከቱበት፤ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ሃይማኖት የጠበቁበት ወቅት ጭምር እንደነበርም ይነገራል።
ንጉሡ በዚህን ወቅት ነበር የዚህን ታላቅ ድል መታሰቢያ እና የፈጣሪን ምስጋና ለትውልድ ለማቆየት ሲሉ በኖራ ግንብ ጥበብ የታነጸውን የደምጎርሳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያሠሩት።
ይህ ሕንፃ የድንጋይ እና የኖራ ድምር ውጤት ብቻ ሳይኾን የፈታኝ ዘመናት ጽናት እና የጀግንነት ሕያው ምልክት ኾኖ እስከ ዛሬ ድረስ በክብር ቆሟል።
👉 የንጉሡ ሕያው አሻራዎች እና ንዋያተ ቅድሳት
ደምጎርሳ ጊዮርጊስ የሃይማኖት ቦታ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ያለፈውን የታሪክ ገጽ ከዛሬው ትውልድ ጋር የሚያገናኝ የቅርስ ግምጃ ቤት ጭምርም ነው።
ወደ ቅዱስ ስፍራው ዘልቀው ሲገቡ የአጼ ገላውዲዮስ ለቦታው የሰጡትን ታላቅ ክብር እና ማስታወሻ የሚያበስር በስማቸው የተቀረጸ ታሪካዊ ማህተም እንደሚገኝ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቤተ መጻሕፍት ቡድን መሪው ግርማቸው ሙሉጌታ ተናግረዋል።
የንጉሡ ግርማ ሞገስ የነበረው አልባሳት (ካባ) እና ይተኙበት የነበረው የአልጋ እግር (ሸንኮር) እስከ ዛሬ ድረስ በጥንቃቄ ተመዝግበው እና በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ ብለዋል። ቤተክርስቲያኑ መንፈሳዊ ልዕልናቸውን እና ጥንታዊ የብራና እና የብረት ጥበብን የሚያሳዩ በርካታ አስደናቂ ንዋያተ ቅድሳትን በውስጡ አቅፎ ይዟልም ይላሉ።
ደምጎርሳ ጊዮርጊስ በየመንገዱ የሚያልፍ ተጓዥ የሚያየው ታሪካዊ ስፍራ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን ጥንታዊ አሠራር፣ የንጉሣውያንን አሻራ እና የድል አድራጊነት ታሪክ የሚመሰክር ሕያው የታሪክ መዝገብም ነው።
ይህን ድንቅ ቅርስ መጎብኘት እና መጠበቅ ያለፈውን ታሪካችንን ማክበር፣ ለነገው ትውልድ ደግሞ ማንነታችንን ማስተላለፍ ነው።
#አሚኮ #ቱሪዝም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም-18_2019 ዓ.ም
✍️ በቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ!









