የባሕላዊ ሠርግ ማድመቂያው ሆማ ቆረጣ !

0
31
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በባሕላዊ የሠርግ ሥርዓቶች ከሚከወኑ ሁነቶች መካከል ሆማ ቆረጣ አንዱ ነው።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ ነዋሪው ዘላለም ጌቴ ሆማ ክረምት እስከ በጋ የማይደርቅ፣ ቅጠሉ ለምለም የኾነ፣ ሲቀመስ የማይመር እና የማይቆመጥጥ ዛፍ እንደኾነ ነው የገለጹልን።
የዚህ ዛፍ ቅጠል በሠርግ ቀን ጠዋት ላይ የሚቆረጠውም ለተጋቢዎች መልካም ምኞት ለመመኘት እንደኾነ ነው የገለጹልን።
ዛፉም እንደሌሎች ዛፎች በአዘቦት የማይቆረጥ እና በአካባቢው ማኅበረሰብ የሚከበር በመኾኑ ሙሽራም በሠርጉ ቀን መከበር እንደሚገባው ለመግለጽ ነው ብለውናል።
ሁነቱ ሲጀምር በሁለቱ ሙሽሮች አካባቢ የሙሽራ ቤተ ዘመድ የኾነ ቅርብ ሰው ሆማ ለመቁረጥ እንሂድ ለማለት የጥሩንባ ድምጽ ያሰማል ነው ያሉት። ይህን የሰሙ የአካባቢው ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች በባሕላዊ ትዕይንቱ ለመታደም በባሕላዊ ልብስ አምረው እና ተውበው ይሠባሠባሉ ብለዋል።
ከዛም እንጀራ በጨው፣ ድቁስ እና ጠላ ድፍድፍ በጽዋ ተይዞ፤ ሙሽሮች ፈረስ ያላቸው ከኾነ በፈረስ ከሌላቸው ወንዱ በትክሻ ተይዞ ሴቷ ደግሞ ታዝላ በታዳሚው ጭፈራ እና ሆታ ታጅበው ሆማ ዛፍ ወዳለበት ቦታ እንደሚያቀኑ ነው የገለጹልን።
ሆማ ቆረጣው… ሆማ ቆረጣው፣
የወንዱን ጉልበት… ዛሬ አሳየው።
“ሙሽራው መጣ… ጋቢውን ደርቦ፣
ሆማ ሊቆርጥ… ቆሟል ተሰልፎ።
ሆም አበባየ… ሆም …
እየተባለ ሲጨፈር ከቆየ በኋላ ዛፉን ሦሥት ጊዜ ዙረው ወንዱ እና ሴቷ ሙሽራ በየተራ በጽዋ የተያዘውን ድፍድፍ ከእነ እቃው ወደ ግንዱ ይወረውራሉ ነው ያሉን።
ወንዱ ድፍድፍ የያዘውን ጽዋ የግድ እንዲሰበር ማድረግ ይኖርበታል። ያ ካልኾነ እንደሰነፍ ተቆጥሮ ይሳቅበታል ብለዋል። ሴቷ ደግሞ ጽዋውን ላለማሰበር ጥረት ታደርጋለች፤ ይህም የሴትነት ክብሯን በቀላሉ የማትሰጥ የተከበረች ሴት መኾኗን ለመግለጽ የሚደረግ ሁነት ነው ይላሉ።
ከዚህ በኋላ አብረው ያሉ የሆማ ቆረጣ ሁነት ተሳታፊዎች ወዲያውኑ የተወረወሩትን ጽዋዎች ይሰባብሯቸዋል። ከዛም የያዙትን እንጀራ በጨው ድቁስ ይመገባሉ። የታዘለ ሕጻን ቢኾን እንኳ አፉ በምግብ ይቀባል ነው ያሉት።
ከዛም ሆማ ቅጠላቸውን ቆርጠው እየጨፈሩ ወደ ሙሽሮች ቤት ሲመለሱ ቤት ከመድረሳቸው በፊት የጥሩንባ ድምጽ ያሰማሉ። በዚህ ጊዜ በሠርጉ ቤት ያሉ የሙሽራ ቤተሰቦች ሸርጉድ ይላሉ። ማረፊያ ቦታ ይስተካከላሉ፤ በትልቅ ብረት ምጣድ ገንፎ ይገነፋል። ምግብ እና መጠጡ ይዘጋጃል።
የሙሽራ እናት (እናት ከሌለች አክስት ወይም ትልቅ እህት) የእህል መንፊያ ወንፊት በአናቷ ላይ አድርጋ ደጅ ላይ ነው የምትጠብቃቸው። ሆማ ቆራጮችም እየጨፈሩ የያዙትን የሆማ ቅጠል ወንፊቱ ላይ ያስቀምጣሉ። ይህ የሚኾነው እናት ብዙ ነገር መሸከም የምትችል መኾኗን ለማመላከት ነው።
ከዛ ባሻገርም እንደዚህ የለመለመ ቅጠል ትዳሩን ያማረ ያድርገው የሚል ምርቃት ለማስተላለፍ ነው። ሀሳቡን መቀበሏን ለመግለጽም ወንፊቱን በአንድ እጇ ደግፋ እስክስታ ትመታለች።
ጭፈራ እና ሆታው ካበቃ በኋላ ከሌላ ምግብ በፊት በሙሽራ መሪነት ቅድሚያ የተገነፋው ገንፎ ይበላል። ይህም በጭፈራ እና በሆማ ቆረጣ ጉዞ የደረቀ ጉሮሮን ለማለስለስ በሚል ነው። ከዚያም ሌሎች ምግቦችን መመገብ ይቀጥላል።
ሙሽራ እና ሚዜም ለዋናው ሠርግ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ በሠርጉ ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ የሰርጉ ዋና ትዕይንት ይቀጥላል ነው ያሉን። ሁነቱ ቀደም ሲል በሚኖሩበት አካባቢ በስፋት ይከወን የነበረ ቢኾንም ከአስር ዓመት ወዲህ ግን እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ነው የገለጹት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴት ባለሙያ በልስቲ ውቤ ሆማ ቆረጣ ባሕላዊ የሠርግ ኹነት የእርስ በእርስ ግንኙነትን እና መተሳሰብን የሚያጠናክር በጎ እሴት መኾኑን ነግረውናል። የመልካም ምኞት መግለጫነቱም በጎነትን እንደሚያስተምር ነው የገለጹት።
ሆማ ቆረጣን ጨምሮ ሌሎች ጠቃሚ ባሕሎች እና እሴቶችን ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጥናት በማድረግ በህትመት እና በዲጂታል አማራጭ ማደራጀታቸውን ነግረውናል። ከማደራጀት ባሻገር የማልማት እና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሆማ ዛፍ የመጥፋት ባሕሉ ላይ ተግዳሮት እየገጠመው ነው ያሉት ባለሙያው የዛፉ መጥፋት ባሕሉ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል።
ባሕል ሕይወት የሚኖረው ደግሞ ሲተገበር እንደኾነ ነው የገለጹት። ከባሕል ተቋሙ ባሻገር አካባቢ ጥበቃን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here