ባለ ኅብረ ቀለሙ ትስኪ ፏፏቴ

0
12

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ትስኪ ፏፏቴ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዳንግላ ወረዳ ውስጥ ከዳንግላ ከተማ በ36ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአለፋ ካቻ ቀበሌ ይገኛል።

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዳንግላ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቦጋለች ፈንታሁን በወረዳው በርካታ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ የቱሪስት ሀብቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከድንቅ ተፈጥሮ ሀብቶች መካካል ትስኪ ፏፏቴ አንዱ እንደኾነም ጠቅሰዋል።

ትስኪ ፏፏቴ ዙሪያውን በዛፎች የተከበበ ዓመቱን ሙሉ የለመለመ ተፈጥሮ ያለበት መኾኑን ተናግረዋል።

ትስኪ ፏፏቴን የሚፈጥሩት “አዊሲ” እና “ግዛኒ” የተባሉ ሁለት ትልልቅ ወንዞች ናቸው ብለዋል። እነዚህ ወንዞች ከየሚመነጩበት ሥፍራ ተነስተው ረጅም ርቀት ሳይገናኙ
ትይዩ ኾነው የመንትያ ወንድማማች ጉዞ ይቀጥላሉ።

ጎን ለጎን እየተያዩ በድንቅ ተፈጥሯዊ ሥነ ሥርዓት
ከፈሰሱ በኋላ አፋፉ ላይ አንድ ላይ ይገናኛሉ። ከዚያም ጥልቅ ወደኾነ ገደላማ ሥፍራ በግሩም ፍሰት ሲወርዱ የትስኪን ፏፏቴ ይፈጥራሉ።

ፏፏቴው ነጎድጓዳዊ ድምጽ ከመፍጠሩ ባለፈ የሚረጨው ውኃ አካባቢው በነጭ ጭጋግ እንዲሸፈን ያደርገዋል። በፏፏቴው አካባቢ ኾነው ቀና ሲሉ በፏፏቴው የሚፈጠረው ባለኅብረ ቀለም የቀስተ ደመና መቀነት መሰል ምስል ለመንፈስ ሐሴትን ያላብሳል፤ ለዕይታ ትኩረትን ይስባል።

የተመልካችን ቀልብ ማርኮ የማቆየት ኀይሉም ከፍተኛ ነው። ከፏፏቴው ጋር ኅብረ ቀለሙ ተደምሮ ሰማይን በቅርበት የሚያስመለክት ይመስላል። የፏፏቴው ጥልቀት በአማካይ 180 ሜትር ነው ብለዋል።

በአካካቢው በሚገኙ ዛፎች ውስጥ የተለያዩ የዱር እንስሳት መኖሪያቸው አድርገው ዘመናትን ተሻግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ቦታውን ከመዝናኛ ባለፈ ጥበቃም እንደሚያደርጉለት ነው የገለጹት።

በፏፏቴው፦

🌴የተለያዩ በርካታ ሀገር በቀል ተፈጥሮአዊ ዛፎች

🕊70 በላይ የሚኾኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኙበታል።

🐆የተለያዩ የዱር እንስሳት እንደ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ዠንጀሮ፣ ጥርኝ፣ ቀይ ቀበሮ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ከፏፏቴው ፊት ለፊት የሚገኘው ሸለቆ እጅግ ውብ በኾነ የተፈጥሮ ደን ያጌጠ አውሮኘላን ላይ ኾኖ መሬትን እንደ መመልከት የሚመስል ሌላ ውብ ገፀ ምድር ያስመለክታል ብለዋል።

የተፈጥሮ ፏፏቴው የቱሪስት መስህብ ስፍራ ብቻ ሳይኾን ለሌሎች የልማት ሥራዎች ሊያገለግል የሚችል ሀብት መኾኑንም ተናግረዋል።

ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ፏፏቴ ባለፉት ጊዚያት የቱሪዝም መዳረሻ በመኾን የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ሲጎበኙት እንደነበር አንስተዋል ። አሁን ላይ ቦታውን ለማልማት ወቅታዊ ችግሩ ፈተና እንደኾነ ተናግረዋል።

በቀጣይ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ይሠራልም ብለዋል። የዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባለቤት የኾነውን ትስኪ ፏፏቴን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here