እምቅ የታሪክ እና የቅርስ ባለቤቱ መልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን

0
16
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታሪካዊ አድባራት መካከል
የመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው።
ቤተ ክርስቲያኑ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በመንቆረር ክፍለ ከተማ ይገኛል። የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ የጎጃም ገዢ ከነበሩት ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ጥልቅ ቁርኝት እንዳለው ታሪክ ያስረዳል።
የመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ዋና አሥተዳዳሪ መላዕከ ፀሐይ መምህር መላክ ጤናው አጼ ዮሐንስ በ1872 ዓ.ም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጎጃምን እንዲያሥተዳድሩ ሹመት እንደሰጧቸው አስታውሰዋል።
በዚያ ዘመን አጼ ዮሐንስ አራተኛ ከእርሳቸው ጋር ከነበሩ አራት ጽላቶች መካከል የቅዱስ ማርቆስን ጽላት ለንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ሰጡ። የቅዱስ ማርቆስ ታሪክም ከዚህ ይጀምራል።
አሁን ደብሩ ካለበት ቦታ ሁለት የተመሰቃቀሉ የግራር ዛፎች እና ከዛፎች ስር ሁልጊዜም የማይጠፍ ሁለት አንበሶች እንደነበሩ ነግረውናል።
ከዚያም ንጉሡ በቦታው ላይ ጸሎት ካስደረጉ በኋላ መልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከል አደረጉ ብለዋል።
የከተማዋ ስም ደብረ ማርቆስ ተብሎ እንዲጠራ ለሕዝቡ አዋጅ አስነገሩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ ደብረ ማርቆስ ተብላ አየተጠራች መኾኑን ነግረውናል።
የወቅቱን ጥበብ የሚገልጡ፤ ታሪክን የሰነዱ እና ዓይን የሚስቡ የግድግዳ ላይ ስዕሎች መኖራቸውንም ነግረውናል። በጥንታዊ ኪነ ሕንጻ አሠራር መገንባቱንም ገልጸዋል።
በውስጡ ከሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል፦
👉 የቀደምት ሊቃነ ጳጳሳት አልባሳት፤
👉 ንጉሡ በቤተ መንግሥት ይገለገሉበት የነበሩ ዕቃዎች፤
👉 ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት፤
👉የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እና ባለቤታቸው ጸሎት ያድረጉበት መቀመጫ ወንበር እና የንጉሡ አጽም ይገኛሉ።
የደብሩ ዓመታዊ ክብረ በዓልም በየዓመቱ ሚያዝያ 30 በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የመዳረሻ ልማት ባለሙያ በላቸው አስማረ በደብሩ የሚገኙ ቅርሶች ተመዝግበው ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በጀት በበመደብ የጥገና ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል። ቅርሶችን ከመጠበቅ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚያዝያን በማርቆስ በተለያዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት እየተከበረ መኾኑን ተናግረዋል። ዘንድሮም በዓሉ ከሚያዝያ 27 እሰከ 30/ 2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
እንግዶችም በዕለቱ በመገኘት በዓሉን እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here