እንሳሮ – ተፈጥሮ የቸራት የታሪክ አድባር

0
24
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የእንሳሮ ወረዳ የተፈጥሮ ጥበብ እና የታሪክ ክብር መገኛ ነው። ከመንዝ እና ከጅሑር አቅጣጫ ቁልቁል የሚወርደው የጀማ ወንዝ ምድሩን እያረሰረሰ ልዩ ለምለምነትን ያጎናጽፈዋል።
የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ከኮከብ መስክ እስከ ጀማ ወንዝ ድረስ እጅግ ማራኪ እና ለዕይታ የሚስብ ነው። አካባቢው የተራራማ እና የረባዳ ስፍራዎች ድብልቅ በመኾኑ ለተመልካች እርካታን ይለግሳል።
ምንም እንኳን አብዛኛው መሬት ወጣ ገባ እና ቆላማ ቢኾንም ውበቱ ግን የሰውን ህሊና የሚያድስ እና የሚመስጥ ነው። ተፈጥሮን ለማድነቅ እና ራስን ለማደስ እንሳሮን መጎብኘት ተመራጭ የሚያደርጓቸው የመስህብ የስበት ስፍራዎች በዚሁ አካባቢ ሞልተዋል።
እንሳሮ በበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ የመስህብ ሀብቶች የታደለች ድንቅ ምድር መኾኗን የወረዳው ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ግዛቸው ቢያዝን ተናግረዋል። የሮቢ ወንዝ የሚፈጥረው ፏፏቴ ደግሞ የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ የሚታወቅ ነው። ወንዙ በጉዞው ላይ ሁለት አስደናቂ ፏፏቴዎችን እንደሚፈጥርም ነግረውናል።
✍️ ወፊ ፏፏቴ፦ ከ200 ሜትር በላይ ከፍታ ላይ ቁልቁል ይወረወራል። ስያሜውንም ያገኘው ከርዝመቱ የተነሳ ወፍ እንኳን የማይደርስበት ተብሎ ስለሚታሰብ ነው ይላሉ።
✍️ መጣያ (መጋረጃ) ፏፏቴ፦ 50 ሜትር ርዝመት እና 30 ሜትር ስፋት ያለው ይህ ፏፏቴ በክረምት ወቅት ነጭ አረፋ ደፍቆ በሚፈጥረው ጭጋግ ለአካባቢው ለምለም ዕፅዋት ዘወትር እርጥበትን ይለግሳል።
✍️ የቡርቃ መዋኛ ገንዳ:- በተራራማው ጉዞ ለደከመው ተጓዥ ከከርሰ ምድር በሚፈልቅ ቀዝቃዛ ውኃ የሚሞላው መዋኛ ገንዳው አካላዊ እና መንፈሳዊ ዕረፍትን የሚሰጥ ሌላው የወረዳው ድንቅ በረከት ነው።
እንሳሮ የተፈጥሮ ብቻ ሳይኾን የታሪክ እና የሃይማኖት አድባርም ናት።
✍️ አባርኮ ዋሻ:- ቀደምት አባቶች በጦርነት ወቅት እንደ መሸሸጊያ ይጠቀሙበት የነበረው እና በፊልም ቀረጻ ጭምር የሚታወቀው የወረዳው የታሪክ አሻራ ነው።
እንሳሮን ለየት ባለ መልኩ የጎብኝዎች መዳረሻ ሊያደርጓት የሚችሉ:-
👉 እንደ ሰቃ መድኃኒዓለም ገዳም፣
👉 ምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳም
👉 ጆር ሥላሴ የወንዶች አንድነት ገዳም ይገኛሉ። ከ2015 ዓ.ም በፊት በሳምንት እስከ 15 በሚደርሱ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በሚመጡ ጎብኝዎች ስትጎበኝ መቆየቷን ጠቁመዋል።
የውጭ ሀገር አምባሳደሮችም የሚጎበኟት እንሳሮ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በጎብኝዎች ቁጥር ላይ መቀዛቀዝ ታይቶባት መቆየቷንም ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ መዳረሻዎች የመንገድ፣ የመብራት እና የውኃ መሠረተ ልማቶች የተሟሉ በመኾኑ ወረዳው ዘርፉን ዳግም ለማነቃቃት በትኩረት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
አባርኮ ዋሻን ለማልማት ዕቅድ ተይዟል። የግል ባለሀብቶች በሎጅ፣ በሞቴል እና በሆቴል ግንባታ ዘርፍ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here