ሞልቶ ከሚፈሰው የቁንጅና ጀርባ ባሕላዊ አለባበሶች ኀይል ኾነው አሉ።

0
26

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከእያንዳንዱ ግርማ ሞገስ ጀርባ አጊያጊያጦች ትልቅ ሚና አላቸው። “ልብሴን ነውር በለው” ሲል የአበው ብሂል አለባበስ እና አጊያጊያጥ ክብርን ያጎናጽፉ ዘንድ አጽንኦት ለመስጠት ነው።

በተለይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሞልቶ ከሚፈስ የውበት ሰገነት ጀርባ ባሕላዊ የአለባበስ ሁኔታዎቻችን ወደር የለሽ ምስጢሮች ናቸው።

በዚህ ጽሑፍ ታድያ የራያ ሴቶች ድንቅ ባሕላዊ አለባበስን በጨረፍታ እንቃኛለን።

ወጣት ሃይማኖት ኃይሌ በራያ ቆቦ ወረዳ የባሕል ቡድን አባል ናት።
የራያ ማኅበረሰብ በደመቀ ባሕሉ ኢትዮጵያን ያስዋበ ማኅበረሰብ ነው ብላናለች። እኛ ራያዎች ለባሕላዊ አለባበሳችን ልዩ ትርጉም የምንሰጥ ሕዝቦች ነን ስትልም ገልጻለች።

በራያ ሴቶች ዘንድ አለባበሳችን ያገባች፣ ያላገባች እና የእናቶች ተብሎ የራሱ መለያ ኖሮት የምንደምቅባቸው አልባሳቶች አሉን ነው ያለችው።

ልጃገረዶች አፈሳሶ፣ ጋሜ እና ቃሪሶ በተሰኙ የጸጉር አሠራሮች ታጅበን፤ ትፍትፍ እና ጥርቅ የሚባሉ ቀሚሶችን ስንለብስ ውበታች ከነበረው ላይ የበለጠ ይጎላል ትላለች።

ባሕላዊ አልባሳት ራያ ላይ በቀልድ የማይታይ እና ትኩረት እንደሚሰጠው ነው የገለጸችው። ባሕላችን ሰፊ እና ጥልቅ ነው ስትልም አጫውታናለች።

በራያ ቆቦ ወረዳ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ውስጥ የባሕል እሴት ባለሙያው ደሳለው ፈንታው የራያ ሕዝብ ጥልቅ የኾኑ ባሕሎች እና እሴቶችን የታደለ ሕዝብ ነው ብለዋል። አለባበስ በራያ ዘንድ እንደየ ዕድሜ ክልሉ ተከፍሎ የየራሱ ማጌጫ ያለው እንደኾነም ገልጸዋል።

በልጃ ገረዶች አለባበስ ዘንድ በትፍትፍ ቀሚስ ላይ የተለያዩ ውበት ያላቸው ክሮች ትርጉም እና ጌጥ በሚሰጥ መንገድ ተጨምረው ይጌጡበታል ብለዋል።

በእናቶች ዘንድ ደግሞ ጥብቆ እየተባለ የሚጠራው የቀሚስ አይነት ልዩ ግርማ ሞገሳቸው ነው ብለዋል። ጥብቆው በተለያየ ዲዛይን እንዲዋብ ይደረጋል ነው ያሉት። ያን ለብሰው የሚወጡ እናቶች ግርማ ሞገስን ተጎናጽፈው ይታያሉ ብለዋል።

ባሕልን፣ እሴትን እና ማንነትን የሚገልጹ ነገሮችን በጥብቆው ላይ እንደሚሰፉበትም አንስተዋል። ገላጭ ኾኖም ይጠለፋል ነው ያሉት። አለባበሱም ኾነ አጊያጊያጡ የራሱ ትርጉም ያለው እንደኾነም አንስተውልናል። ከቆዳ የተዘጋጀ ጥልፍልፍ ጫማ ለሴቶች አለባበስ ውበትን እንዲደርቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በልጃገረዶች ዘንድ ከአልባሳቱ በተጨማሪ ሹርባ፣ አንድ ግራ የተሰኘ እና የዓሳ ስሪት የጸጉር አሠራሮች የማይቀሩ ናቸው ይላሉ። አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ክር ከጸጉሩ ላይ እንደሚጨምሩበትም አንስተዋል። “ያኔ ውበት ሞልቶ ይፈሳል” ነው ያሉት።

ድኮት ከእጅ ላይ፤ ድንብል ከአንገት ላይ እና የወግ ማዕረግ እቃወችን አንጠልጥለው ሲጓዙ ግሩም ቁንጅና ይታያል ባይ ናቸው።

የባሕል እና ቱሪዝም ተቋም ባሕሉ እንዳይበረዝ እንዳይከለስ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል ባለሙያው። ባሕሉ እንዲሠነድም ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸውልናል።

ዶክተር ድርቧ ደበበ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር ናቸው። አልባሳት ሀገረሰባዊ የእጅ ሥራ ጥበብ ውስጥ የሚጠና ነው ብለዋል። አለባበስ አንድ ማኅበረሰብ በርካታ ዘርፍ ያለውን ማንነቱን የሚገልጽበት እንደኾነም ገልጸዋል።

አልባሳት በአንድ ዘመን የነበረን ማኅበረሰብ ባሕል፣ የአኗኗር ዘይቤውን፣ ማንነቱን፣ ወጉን፣ ታሪኩን፣ ልማዱን እና ፍልስፍናውን ማሳወቂያ ኀይል ነውም ብለዋል።

📸ፎቶ፦ ከአሚኮ ዲጂታል ፋይል

#አሚኮ #ባሕላዊ_አለባበስ #ራያ #አማራ #ኢትዮጵያ🇪🇹

በሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here