ጮቄን መጠበቅ ዓባይን መጠበቅ ነው !

0
24

 

ባሕር_ዳር: ሰኔ 23/2018 ዓ.ም ጮቄ ተራራ የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ፤ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ ደጋፊ ነው። ከባሕር ወለል በላይ 4 ሺህ 88 ሜትር ከፍታ ያለው ሲኾን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ ተራራዎች መካከል አንዱ ነው።

በምሥራቅ ጎጃም በስምንት ወረዳዎች እና በምዕራብ ጎጃም ዞን በአንድ ወረዳ በጥቅሉ በዘጠኝ ወረዳዎች የሚዋሰነው ጮቄ 53 ሺህ 558 ሄክታር በላይ መሬት ጠቅላላ ስፋት እንዳለው የአማራ ክልል ደን እና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል።

እነማይ እና እናርጅ እናውጋ፣ ሰዴ፣ ቢቡኝ፣ ማቻከል፣ ስናን፣ ደባይ ጥላት ግን እና በሌሎች ወረዳዎች ይዋሰናል። ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለው ይህ ቦታ በተለይም በክረምት ወቅት ከሳምንት በላይ በበረዶ የሚሸፈንበት ወቅት ነበር ። አሁን አሁን ግን የበረዶ ግግሩ እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

23 ትላልቅ ወንዞች እና 273 ትናንሽ የዓባይ ገባሮች ከሥሩ የሚፈልቁበት የውኃ ጋን መኾኑ እውነትም ጮቄ ያሰኘዋል። በተለምዶ “ጮቄ” የሚባለው ውኃ የሚበዛበት አካባቢ በመኾኑ ነው።

ከ85 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች እንዲሁም በርካታ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የአዕዋፋት ዝርያዎች መገኛ ነው። በተለይም ጅብራ የተሰኘው የተራራ ላይ ድንቅ ተክል ውበት ሰጥቶት ይታያል።

ጮቄ በጣም ሰፊ ከመኾኑ የተነሳ ገና ብዙ ያልታወቁ ዋሻዎች፣ ጥንታዊ መኖሪያዎች እና ያልተዳሰሱ አስደሳች የተፈጥሮ መስኅቦች እንደሚኖሩት ይታመናል። የጮቄ ተራራ ልዩ ውበት እና ተፈጥሯዊ ፀጋ የተላበሰ በመኾኑ ለቱሪስት መዳረሻነት ያገለግላል።

በተራራው እምብርት የሚገኘው የጮቄ ተራሮች ኢኮሎጅ በተፈጥሮ ጥበቃ እና በማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም ባሳየው ስኬት በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አማካኝነት የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ዕውቅናን አግኝቷል። 6 ሺህ 24 ሄክታር መሬት ተከልሎ እንዲጠበቅ እና እንዲለማ ብሎም ማኅበረሰቡ እንዲጠቀምበት የጮቄ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ተቋቁሞለትም ይገኛል።

ምንም እንኳን የጮቄ ተራራ ለአካባቢው እና ለሀገር እጅግ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብት ቢኾንም አሁን ላይ ከፍተኛ የሰው ሠራሽ አደጋዎች እንደተጋረጡበት መረጃዎች ያሳያሉ።

በአካባቢው ባለው የሰላም ችግር ምክንያት ቁጥጥሩ ባለመጠናከሩ ልቅ ግጦሽ እና ሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ የተራራውን ሥነ-ምኅዳር እያናጋው እንደሚገኝ ተነግሯል። ከተራራው ከፍታ ቦታዎች ላይ የእርሻ መሬት እየተስፋፋ በመምጣቱ የዱር እንስሳት መኖሪያቸውን እያጡ መኾኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ሳይንስ እና ዚኦሎጅ ምሁር “በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የጮቄ ተራራ የዱር እንስሳት እና የሥነ-ምኅዳር ሁኔታ ግምገማ” በሚል የጥናት ውጤታቸው አመላክተዋል።

በተራራው ላይ እየደረሰ ያለው መራቆት በቀጥታ የውኃ ምንጮች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።

በአሁኑ ወቅት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ማዕከላት ተራራውን ከጥፋት ለመታደግ፣ የተፋሰስ ልማት ለማድረግ እና ማኅበረሰቡን ከንብ ማር እና ቱሪዝም አማራጭ ገቢ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረቶችን እንደጀመሩ በጥናታዊ ጽሑፋቸው አመላክተዋል።

📢 ጮቄን መጠበቅ ዓባይን መጠበቅ ነው።

#አሚኮ_ዜና #ChokeMountain #Ethiopia #VisitEthiopia #EcoTourism #ProtectNature #SaveChoke🇪🇹

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here