“የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅኝቶች እና የወሎ አሻራ”

0
133
ኢትዮጵያ የራሷ የኾኑ አራት የሙዚቃ ቅኝቶች አሏት። ባቲ፣ አምባሰል፣ አንቺሆየ፣ ትዝታ ይሰኛሉ።
እነዚህ የሙዚቃ ቅኝቶች የማኅበረሰብ ሀብቶች ናቸው። በሀገራችን የሚከወኑ ሙዚቃዎችም በእነዚህ አራት ቅኝቶች ተቃኝተው ይከወናሉ። የእነዚህ የሙዚቃ ቅኝቶች መፍለቂያው ደግሞ ወሎ ነው።
ወሎ የበርካታ ባሕሎች ባለቤት ነው። ወሎየዎች በፍቅር መኖርን ያውቁበታል፤ አብሮነት መለያቸው ነው። የውቦች መፍለቂያም እንደኾነ ይነገርለታል። ከአፋር፣ ከኦሮሞ ከአማራ እና ከትግራይ ማኅበረሰቦች ጋር በአብሮነት የመኖር የረጅም ልምዱ የእነዚህ አራት ቅኝቶች መፈጠርያ እንዲኾን አስችሎታል።
“ከተማሩ እንደ አካልየ፤ ከተዋጉ እንደ ገብርዬ” የተባለላቸው የመምህር አካለወልድ መፍለቂያም ነው ወሎ።
የባቲ ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ የኾኑት አደም መሐመድ የ”ባቲ “የሙዚቃ ቅኝት በባሕል ከዳበረችው ባቲ ከተማ ስያሜውን እንዳገኘ ይነገራል ብለዋል። ይህ የሙዚቃ ቅኝት የባቲ እና አካባቢው ካለው መልክዓ ምድራዊ ስብጥር እንዲሁም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ለረጅም ዘመናት አብሮ ከመኖር ልምዱ የተፈጠረ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የባቲ ፍቅር፤ የባቲ ውበት ሲገለጽበት የኖረ ቅኝትም ነው ብለዋል። “ባቲ ጎድጓዳ ነው አይታይም ጭሱ በሽንጣም አውቶብስ ከዚያው ካልደረሱ” እየተባለም ቦታው ይዜምለታል ነው ያሉት።
በደቡብ ወሎ ዞን ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ቡድን መሪ የኾኑት ኃይሉ ታደሰ አምሳል የሙዚቃ ቅኝት ከአምባሰል ወረዳ መልክዓ ምድራዊ እና ማኅበረሰባዊ ስብጥር የተሰጠው እንደኾነ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል።
“ይሄማ ውጫሌ፤ ይሄ ቆላማው
ጠይም ልጅ ያበቅላል እንደ ዘንጋዳው”
የተባለለት የውቦች መፍለቂያ ስለኾነ የሙዚቃ ቅኝቱም መፈጠርያውን እዚህ ስፍራ ኾኗል ነው ያሉት።
ዶክተር አስቴር ሙሉ ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት በሚለው መጽሐፋቸው ማሲንቆን በመጠቀም የቅኝቶችን የድምጽ አፈጣጠር አስነብበዋል።
በመጽሐፉ እንደተገለጸውም የድምጾች አፈጣጠር፦
👉 አምባሰልን ቅኝት በመሰንቆ ለማግኘት; አውራጣት ከመቃኛው በአንድ ጣት ርቀት ይቀመጣል። አመልካች ጣት ባለበት ሁኔታ ተዘርግቶ ይቀመጣል፤ መሐል ጣት ከአመልካች ጣት በአንድ ጣት ርቀት ትቀመጣለች፤ ትንሿ ጣት ደግሞ መሀል ጣትን ተጠግተው ይቀመጣሉ ሲሉ አስፍረዋል።
👉 ትዝታ ቅኝትን በመሰንቆ ለማግኘት; ከመቃኛው ስር የሁለት ጣት ርቀት ዝቅ ብሎ አውራ ጣት ይቀመጣል፤ በየጣቶቹ መሐል ደግሞ የሁለት ጣት ያህል ርቀት ክፍተት እየተወ አመልካች፣ መሐል እና ትንሿ ጣት ተዘርግተው ይቀመጣሉ ነው ያሉት።
👉 የአንቺሆየ ቅኝትን በማሲንቆ ለማግኘት ;አውራ ጣት ከመቃኛው የአንድ ጣት ያህል ርቆ ይቀመጣል፤ አመልካች ጣት ከአውራ ጣት ሰፊ ርቀት እንዲፈጠር እስከመጨረሻው ተዘርግታ ትቀመጣለች፤ መካከለኛ ጣት አመልካች ጣትን ተጠግታ ትቀመጣለች፤ ትንሽዋ ጣት ደግሞ ከቀለበት ጣት በአንድ ጣት ርቀት ይቀመጣሉ ብለዋል።
👉 የባቲ ቅኝትን ለማግኘት ደግሞ አውራ ጣት ከመቃኛው የአራት ጣት ርቀት ይቀመጣል፤ አመልካች ጣት እና መካከለኛ ጣት ከአውራ ጣት ተጠጋግተው ይቀመጣሉ ሲሉ በመጽሐፋቸው ተንትነው አስፍረዋል።
✍️ በፈረደ ሽታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here