🍂 በጥቅምት አንድ አጥንት ምን ማለት ነው ? 🍗

0
98

 

ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን የተሻገሩ፣ የማኅበረሰቡን ማንነት፣ እሴት እና የኑሮ ፍልስፍና የሚዘክሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አባባሎች እና ብሂሎች ባለቤት ናት። እነዚህ አጫጭር ግን ጥልቅ መልዕክት ያዘሉ የቃል ግጥሞች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች እና አባባሎች ማኅበረሰቡን በማስተማር፣ ለችግሮች መፍትሔ በማመላከት፣ በመገሰጽ እና አንድነትን በመስበክ ረገድ ትልቅ የጥበብ ምንጭ ኾነው እያገለገሉ ዘመናትን ተሻግረዋል።

ለችግር መፍትሔ ከሚመላክትባቸው ብሂሎች መካከል ዛሬም ሲነገር የሚደመጠው “በጥቅምት አንድ አጥንት” አንዱ ነው።

📚ታዋቂው የታሪክ እና የባሕል ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ በመጽሐፎቻቸው ላይ እንደጠቆሙት የኢትዮጵያ ሕዝብ የወቅቶችን መለዋወጥ ከምግብ ባሕሉ ጋር አቆራኝቶ የመግለጽ ትልቅ ጥበብ አለው። በጥቅምት አንድ አጥንት የሚለው ብሂልም የዚሁ ማሳያ ነው።

❄️ የብሂሉ መነሻ ሁለት ትልልቅ መሠረቶች አሉት። አንደኛው ከተፈጥሮ የአየር ንብረት ጋር የተያያዘ ነው። ጥቅምት ወር የክረምቱ ደመና የሚገለጥበት፣ የጸደይ ወቅት የሚተካበት እና መሬት በአዝእርት የምታጌጥበት፣ አዝመራ የሚሽትበት፣ የደፈረሱ ወንዞች የሚጠሩበት፣ ሌሊት እና ጠዋት የበረታ ቅዝቃዜ የሚኖርበት ከመኾን ጋር የተያያዘ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አጥንት የሚሰበር የሚመስለውን ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሰውነትን የሚያሞቅ እና ኀይል የሚሰጥ የሥጋ ምግብ መመገብ አስፈላጊ መኾኑን ለመግለጽ “በጥቅምት አንድ አጥንት” የሚል ብሂል የቀደሙ አባቶች እና እናቶች መፍጠራቸው ይጠቀሳል።

🥣 በሌላ በኩል ደግሞ “በጥቅምት አንድ አጥሚት” ይባል ነበር ይባላል። ይህም በቅዝቃዜ ወቅት ሰውነትን የሚያሞቅ እና ጉልበት የሚሰጥ አጥሚት መጠጣት ማስፈለጉን ለመግለጽ ይነገር እንደነበር ይገለጻል። በጊዜ ሂደት ግን “አጥሚት” ወደ “አጥንት” ተለውጦ ብሂሉ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል።

🤝በጥቅምት አንድ አጥንት የሚለው ብሂል ሰዋዊ እና ማኅበራዊ እሴቱ እጅግ የጎላ ነው። ከእሴቱ መካከል የአብሮነት ትስስር መፍጠር ነው። አብሮነት ከሚፈጥሩባቸው አጋጣሚዎች ሥጋን ለመመገብ ሲያቅዱ ቅርጫ 🥩 የሚከፋፈሉበት እና ማዕድ የሚጋሩበት ሁነት ይጠቀሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታዋቂው ደራሲ እና ተመራማሪ ፈቃደ አዘዘ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት እንዳሉት ቅርጫ ጥቅሙ ሥጋ መካፈል ብቻ አይደለም። የሰዎች መተሳሰብ፣ የአቅም መደጋገፍ እና የደስታ ሽሚያ ማሳያ ጭምር እንጂ።

በጥቅሉ ጥቅምት ሲጠባ አጥንት መቁረጥ ብቻ ሳይኾን፣ ፍቅርን መጋራት፣ የተጣላን ማስታረቅ እና አብሮነትን ማደስ የኢትዮጵያውያን ውድ ባሕል ነው። በጎ እሴቶችን እና ባሕሎችን እንጠቀምባቸው።

👉በጥቅምት አንድ አጥንት ከሚለው ብሂል ጋር ተያይዞ የሚነገሩ ቃላዊ ግጥሞችን በኮሜንት ያጋሩን?

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!

#በጥቅምትአንድአጥንት #Ethiopia🇪🇹

#የማኅበረሰብእሴት

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_21_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here