ዩኔስኮ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

0
94

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አለም አቀፍ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኔስኮ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት(ዶ.ር) ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ በትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል። የተለያዩ ቅርሶችን በመመዝገብ ቅርሶቹን ጠብቆ የማቆየት እና የመንከባከብ ሥራ ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የዩኔስኮ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሀገር ናት ብለዋል። በዚህም እንደዩኔስኮ የኢትዮጵያ ተወካይ ኩራት ይሰማኛል ያሉት ዶክተር ሪታ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ ቅርሶችን ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ከማስቻሉም ባለፈ ቅርሶቹን የሚጎበኙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግ የአካባቢው ማኅበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሀብቶችን ለአለም ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው በኢትዮጵያ ያሉ ዲፕሎማቶች በሀገሪቱ ያሉ ቅርሶችን እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዩኔስኮ መንግሥት በቅርስ ጥበቃ እና በሌሎች ዘርፎችም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here