ዘመናትን የተሻገረው የራያዎች ድምቀት-ሶለል

0
35
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጋው አልፎ ክረምት ሲተካ የገረጣው መሬት በአረንጓዴ ልምላሜ ይሸፈናል። ምድር ልብሷን ትለብሳለች። ጋራው እና ሸንተረሩ በእጽዋት ያሸበርቃል።
ክረምት ገብቶ፣ ዝናቡም መሬቱን አጥግቦ ከሰነባበተ በኋላ ምድር በሳር በቅጠሉ ትሞሸራለች፣ ዕጽዋትም ማበብ ይጀምራሉ፣ ምድር በአበቦች ትዋባለች። ዝናብ የከረመበት መሬትም ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ጠፈፍ እያለ ሲመጣ፣ ደመናው እየገፈፈ ሲሸሽ፣ ፀሐይም ሙሽራ መስላ ትገለጣለች። በዚህ ወቅትም ልጃገረዶች ዓመቱን ሙሉ ሲናፍቁት የከረሙትን ጨዋታ የሚጫወቱበት የአሸንድየ ቅጠልም ይለመልማል።
ከዛሬ ነሐሴ 16/2017 ጀምሮ የራያ ልጃገረዶች ተውበው፣ አምረው እና ደምቀው የሶለል በዓላቸውን ሊያከብሩም በአደባባይ ተከስተዋል።
👉 የሶለል በዓል መነሻ መሠረቱ
ሶለል በራያ አካባቢ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ድረስ ልጃገረዶች የሚጫወቱት ባሕላዊ ክዋኔ ነው። ባሕሉ ሃይማኖታዊ መሠረት እንዳለውም ይነገራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኀላፊ መምህር ኤርምያስ አዳነ የሶለል ባሕል መነሻው ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለው ይናገራሉ። መምህር ኤርምያስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብሉይ ኪዳን እና በሀዲስ ኪዳን ሃይማኖታዊ መነሻ ጠቅሰው ያስረዳሉ። ይህም ከቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት እና ዕርገት ጋር የሚያያዝ ሰፊ አስተምህሮ እንዳለውም ነው ያመላከቱት። እንደ መምህር ኤርምያስ ገለጻ ልጃገረዶች በጨዋታቸው “አሸንዳ ሙሴ ፈስስ በይ በቀሚሴ” እያሉ የሚያዜሙት ዜማም ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕጽን ወይም ‘እጸ ሙሴ’ን ለማጠየቅ እንደኾነ ያብራራሉ።
ልጃገረዶች ክብ ሠርተው ሲጫወቱ ከመሀል ኾና የምታቀነቅነው ልጃገረድ የእመቤታችን ምሳሌ፣ ተቀባዮች የቅዱሳን መላዕክት፣ በወገባቸው የታጠቁት የአሸንድዬ ቅጠል ደግሞ የመላዕክት ክንፍ መኾኑን ነው መምህር ኤርምያስ ያብራሩት። ወደ ግራና ወደ ቀኝ እያወዛወዙ የሚጫወቱት ደግሞ መላዕክት ክንፋቸውን ከክንፋቸው እያማቱ በፍጹም ደስታ እያመሰገኑ እመቤታችንን ያሳረጉበትን ምሳሌ የሚገልጽ መኾኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በመነሳት የሶለል ባሕል ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ ከዛሬው ትውልድ መድረሱን አመላክተዋል።
👉 የልጃገረዶች ዝግጅት ለሶለል በቆቦ ከተማ ነዋሪ የኾነችውና የሶለል ተጫዋች ወጣት ሃይማኖት ኀይሌ የሶለል በዓል በየዓመቱ በናፍቆት የሚጠብቁት በዓል እንደኾነ ትገልጻለች። እንደ ወጣቷ ገለጻ የሶለል በዓል ከመድረሱ በፊት ልጃገረዶች በቡድን እየተሰባሰቡ አለቃ በመምረጥ ዝግጅታቸውን ይጀመራሉ፡፡ ለአለቃነት የምትመረጠው ልጃገረድም እነሱን የምትቆጣጠር፣ ሲያጠፉ የምትመክርና የምትቆጣ፣ ግጥም የምታወጣ፣ የሚስብ የድምጽ ቅላጼ ያላት፣ ወደ ኋላ ሲቀሩ የምታበረታታ መኾን እንደሚኖርባት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በአለቃዋ ቤት በመሰባሰብም ግጥምና ዜማ እያጠኑ፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እያዘጋጁ ይቆያሉ፡፡ የሶለል በዓልን ለመጫወት የሚጠቀሙት ቅጠል አሸንድዬ በመባል ይጠራል።
ለበዓሉ 2 ወይም 1 ቀን ሲቀረው ወንድ ወጣቶችን አሸንድዬ ከሚገኝበት ስፍራ በመላክ የአሸንድዬውን ቆርጠው እንዲያመጡላቸው ያደርጋሉ፡፡
ልጃገረዶችም የመጣላቸውን የአሸንድዬ ቅጠል በሚፈልጉት መልኩ እየጎነጎኑ ያዘጋጁታል፡፡ ከዚሁ ጋር ባሕላዊ የመዋቢያ ቁሳቁሶችን፣ ጌጣጌጦችን እና አልባሳትንም ጭምር እያዘጋጁ ይሰነባብታሉ።
👉 የሶለል ተጫዋቾች መዋቢያና ጌጣጌጦች
እንደ ወጣት ሃይማኖት ገለጻ የሶለል ተጫዋች ልጃገረዶች መዋቢያቸው ብዙ ነው። የፀጉር አሠራራቸውም በእድሜ ደረጃ እና በትዳር ሁኔታ ይለያያል። ሕጻናት ልጆች በአካባቢው አጠራር “ጋሜ” እና “ቃሪ” የሚባሉትን የፀጉር ስሬት ይሠሩታል፡፡ “አሳስር” እና “አፈሳሶ” የሚባለው ደግሞ እድሜአቸው ከ14 እስከ 20 ዓመት ያሉት ልጃገረዶች የሚሠሩት ነው። “እጩኝ፤ ለትዳር ደርሻለሁ” እንደማለትም ነው። ጊጫ፣ አለባሶ፣ ውስጠ ወይራ፣ ሹርባ፣ ጎበዝና ቆንጆ እና ሌሎች መጠሪያዎች ያሏቸው የፀጉር አሠራሮችንም ሌሎች ሴቶች በበዓሉ ሰሞን ተሠርተው ይዋባሉ፡፡ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ፀጉራቸውን ቅቤ ይቀባሉ። ቆንጆ ውብ እንዲኾኑም ዐይናቸውን ይኳላሉ፤ ይዋባሉ። ትፍትፍ፣ አምሾ፣ ዋሾ ሸማ የሚባሉትንም አልባሳት ይለብሳሉ፡፡ በተለያዩ ክሮች ያሸበረቀ መቀነት ወገባቸው ላይ ሸብ ያደርጋሉ፡፡ የብር ድንብል ጌጥ ከደረታቸው ላይ ያደርጋሉ።
👉 የሶለል ጨዋታው ክዋኔ ነሃሴ 16 በጠዋቱ ልጃገረዶች አምረውና ደምቀው ከየቤታቸው ይወጣሉ። የመጀመሪያ ተግባራቸውም ቤተ ክርስቲያን ሄደው ጸሎት ማድረስ እና ፈጣሪን ማመስገን ነው። ከዚያም ጨዋታቸውን የሚጀምሩትም በአካባቢያቸው ከሚገኝ ከዕድሜ ባለጸጋ አዛውንቶች ቤት ነው።
ልጃገረዶቹ የበዓሉ ድምቀት በኾነው በራያ ትፍትፍ ልብስ ደምቀው፣ የእግር አልቦ እና የፀጉር ሥሬት አምረው፣ ተውበው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ። ወገባቸው ላይ የታጠቁትን የአሸንድዬ ቅጠል በማወዛወዝ ረዘም ብሎ በሚደመጠው ድምጻቸውም “ሶለል…ሶለል…” እያሉ የሚያስደምመውን ዜማ ያዜሙታል፡፡ የአሸንድዬውን በወገባቸው ታጥቀው በኅብረት እና በተረጋጋ ስሜት ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ፣ ደግሞም በዝግታ ወገባቸውን ሲያንቀሳቅሱት፣ አብሮ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ እያወዛወዙ ይከውኑታል፡፡ በዚህ በዓል የተለያዩ ግጥሞችን ከዜማ ጋር በማዋሐድ ቤት ለቤት እየዞሩ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑበታል፡፡ የአካባቢውን ዕሴት፣ ትውፊት፣ፍቅርን፣ ተስፋን ይገልጹበታል፤ ውበትን፣ ጀግንነትን ያወድሱበታል።
👉የወንዶች ተሳትፎ በሶለል ጨዋታ የሶለል በዓል ልጃገረዶች የሚጫወቱት ክዋኔ ቢኾንም ወጣት ወንዶችም ጭምር አምረውና ደምቀው የሚወጡበት ቀን ነው፡፡ ወንዶቹ እንደ እርቦ ወይም ጋቢ፣ ከታች ግልድም ያደርጋሉ። ጥርቅ የሚባለውን ከበሬ ቆዳ የተዘጋጀ ጫማ ይለብሳሉ።
በጥርሳቸው ላይም ሲዋክ (የጥርስ መፋቂያ)፣ ፀጉራቸው ላይ ሚዶ ሰክተው፣ በእጃቸው በትር በመያዝ ሶለል ከሚሉ ልጃገረዶች እየተከተሉ ይጨፍራሉ፡፡ ጅራፍ ይዘው እያጮሁ ከኋላቸው እየተከተሉ የሚያጅቡ ወንዶችም አሉ። በዚህ አጋጣሚ ኮበሌው የሚፈልጋትን ቆንጆ ልጃገረድ ካለች ለፍቅር ያጫታል። ከኋላ በመኾን የአሸንድዬዋን ቅጠል በጥሶ በመውሰድ ፍቅሩን ይገልጽላታል፡፡ እሷም ዞር ብላ በአይኗ ትቃኘዋለች። በፈገግታ ስሜት ፈቃደኝነቷን ትገልጽለታለች ፡፡ በዚህ መልኩም ይተጫጫሉ፡፡ የሶለል ባሕላዊ ጨዋታን ከ10 ዓመት በላይ እየተጫወቱ ያሳለፉት ወይዘሮ አዝመራ ሞላ አሁን ላይ የሶለል ጨዋታ የሚጫወቱ ልጆች እንዳሏቸው ነግረውናል። ባሕላዊ ትውፊቱ ከጥንት ጀምሮ የነበረ እና ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የቀጠለ መኾኑን አንስተዋል። ልጆች በሶለል ባሕላዊ ጨዋታ ቁጥጥር እንደማይደረግባቸውም ነግረውናል።
የፈለጉትን ነገር የሚያደርጉበት ተናፋቂ ወቅት ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት። ወላጆችም የመዋቢያ እና የሚያጌጡበትን ሁሉ የማሟላት ግዴታ አለባቸው ነው ያሉት። በሶለል በዓል የሚዜሙ ዜማዎችና ግጥሞች እንዳሉም ገልጸዋል።
👉በሶለል ጨዋታ የሚዜሙ የግጥም ስንኞች(ለቅምሻ)
በሶለል ጨዋታ ልጃገረዶች በስፋት ከሚጠቀሟቸው የግጥም ስንኞች የተወሰኑትን ለአብነት ለማንሳት ያክል:
በጋራ ኾነው ሲጫወቱ:-
“አሸንድዬ አሸንዳ አበባ፤ እርግፍ እንደ ወለባ፤
አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ፣ ፍስስ እንደ ቀሚሴ” … እያሉ ይጨፍራሉ።
የሶለል ተጫዋቾች በየቤቱ እየሄዱ ደግሞ:-
“ሶለል ብየ መጣሁ
ሶለል ብዬ፣
ጌቶች አሉ ብዬ…
ይኼ የማን ነው ቤት፣ የጸዳ የኮራ፣
ከነ ባለቤቱ፣ ስሙ የተጠራ…” እያሉ ያዜማሉ።
ሶለለል …ሶለለል…
ኧረ አበየ እገሌ የጌታው ልጅ ጌታ፣
ጠጠር አስመስሎ በብር የሚማታ።
“ሸሙናየ…”ሸሙናየ…
ሸሞንሟና ኩታ አሠርቼልህ፣
የማንን ድሪቶ ትጎትታለህ…
… ሸሙናየ” እያሉ አባዎራውን ያወድሳሉ።
“ሶለለል…ሶለለል
ከጎታ ላይ ኾና፣ ታሽካካለች ዶሮ፣
ኧረ እነየ እገሌ፣ ደልዳላ ወይዘሮ …ሶለለል” እያሉ ደግሞ እማዎራዋን ያወድሳሉ፡፡
እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ በእያንዳንዱ የጨዋታ ኹነት የራሱ ግጥምና ዜማ አለው። የሶለል ተጫዋቾችም በየቤቱ እየተዘዋወሩ በእናቶች፣ በአባቶች፣ በሽማግሌዎች ይመረቃሉ፤ ስጦታም ይበረከትላቸዋል፡፡
“ከብረው ይቆዩ ከብረው፣
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው፣
ሰላሳ ጥጆች አስረው፣
ሦስት አዳራሽ ቤት ሠርተው፣
ከብረው ይቆዩ ከብረው።” የሚለው ደግሞ የምስጋና እና የመሠነባበቻ ዜማቸው ነው፡፡
በየቤቱ ተዘዋውረው ሲጨፍሩ የሚሰጣቸውንም ገንዘብ ወይም ሌላ ስጦታ ሰብስበው በአለቃቸው ቤት ድግስ ያዘጋጃሉ፡፡ የአካባቢውን አዛውንቶች ጠርተው በመጋበዝ ይመረቃሉ፡፡ ሶለል የራያዎቹ ልዩ መልክ፣ ውበት፣ ድምቀት ነውና በዓላቸውን በራያ ምድር ተገኝታችሁ የሶለል ሙሽሮችን አድምቋቸው እንላለን፡፡
ዘጋቢ፡- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here