ለግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

0
29

ባሕር ዳር: መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል። በበዓሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ይገኛሉ። በዓሉ የጎብኝዎችን ፍሰት የሚጨምር ነው።

የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሥተዳዳሪ አባ ብሥራተ ገብርኤል ክፍለ ማርያም የ2018 የመስቀልን እና የግሼን ደብረ ከርቤ በዓል ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

አባ ብሥራተ ገብርኤል እንዳሉት የደብሩ አሥተዳደር ሰበካ ጉባኤ፣ ማኅበረ ካህናቱ እና የአጥቢያው ምዕመናን በተለየ ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ ነው።

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች በድምቀት እንደሚከበር ያነሱት አባ ብሥራተ ገብርኤል ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ደግሞ በዓሉ የተለየ ድምቀት አለው ብለዋል።

በበዓሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እና ከውጭ የሚመጡ አማኞች እና ጎብኝዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል። ለጎብኝዎቹ ምቹ የኾነ መሥተንግዶ ለማቅረብ እየሠራን ነው ብለዋል። ለንግሡ ለሚመጡ ምዕመናን ማረፊያ የሚኾን ሰፊ ቦታ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ መንገዱን ምቹ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንገዶች አሥተዳደር አማካኝነት መንገዱን የመጠገን ሥራ እንደተሠራ ተናግረዋል፡፡
ለመኪኖች መቆሚያ የሚኾኑ አራት መናኸሪያዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚገኙ ምዕመናን እና ጎብኝዎች በዓሉን በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሣ የግሸን ደብረ ከርቤ እና የመስቀል በዓላት በድምቀት እና በሰላም እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ለበዓሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንግዶች ይመጣሉ፤ ለዚህም ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡም በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባሕሉ እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጎብኝዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲያከብሩ እና ሌሎችን እንግዶች እንዲስቡ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ሰላምና ጸጥታው አስተማማኝ እንዲኾን ሁሉም በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here