‎ጥንታዊው ሳርዝና ሚካኤል ውቅር ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን

0
37
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የሰሜን ወሎ ዞን ብዛት ያላቸው በተለያዩ ጊዜያት የታነጹ እና የሀገሪቱ ቀደምት ሥልጣኔ ማሳያ የኾኑ የአለት ላይ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መገኛ አካባቢ ነው፡፡ ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሳርዝና ሚካኤል ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡
‎ሳርዝና ሚካኤል ውቅር የአለት ላይ ፍልፍል ቤተክርስቲያን በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከተራራ ሥር ሳቢ እና ማራኪ በኾነ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚገኝ የሀገር ቅርስ ነው፡፡ ከላሊበላ ከተማ ወደ ሰቆጣ በሚወስደው መንገድ 17 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ በስተግራ በኩል ገባ ብሎ በስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
‎የሳርዝና ሚካኤል ቤተክርስቲያን አሥተዳዳሪ ቄስ ሀብቴ ካሳነው ቤተክርስቲያኑ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት መመሥረቱን ተናግረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከአለት ተፈልፍሎ የተሠራ ሲኾን መቅደስ፣ ቅድስት፣ ማህሌት እና ቅኔ ማህሌት ክፍሎች አሉት ነው ያሉት፡፡
ፍልፍል ቤተ ክርስቲያኑ አራት የውጭ እና አምስት የውስጥ በጥቅሉ ዘጠኝ አምዶች አሉት፡፡ ሦስት በሮች እና ስድስት መስኮቶች ያሉት ሲኾን የአሠራር ጥበቡ እና ጥንታዊነቱ ለየት ያለ እና አስደናቂ ቅርስ አድርጎታል ብለዋል፡፡
‎በውስጡም በርካታ ዕድሜ ጠገብ፣ ታሪክ ነጋሪ እና ሃይማኖታዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቁጥራቸው ከ70 በላይ የሚኾኑ የብራና መጻሕፍት፣ ጥንታዊ መሥቀሎች እና ከብረት የተሠራ የአጼ ካሌብ ማሕተም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቅርሶቹም በባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት መመዝገባቸውን ገልጸውልናል፡፡
‎ከብራና መጻሕፍቶች ውስጥ በብዙ ቦታዎች የማይገኙ ድጓ እና መጽሐፈ ሲኖዶስ የመሳሰሉ ታላላቅ ሃይማኖታዊ መጽሐፍት በሳርዝና ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
‎በተለያዩ ጊዜያት በዕድሜ ብዛት እና በሌሎች ምክንያቶች ቋሚ ቅርሱ ጉዳት ደርሶበት ጥገና ተደርጎለታል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ለቅርሱ የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ እየተሠራለት መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
‎በላስታ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ሙሉ ታደሰ የሳርዝና ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን በላስታ ወረዳ ከሚገኙ ዋና ዋና የመስህብ ሀብቶች አንዱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከፊል ውቅር ማለትም ከጋራ ጋር ተያይዞ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው ብለዋል፡፡ ከ485 እስከ 536ዓ.ም በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግስት እንደተሠራ ይነገራል ነው ያሉት፡፡
‎በጥንታዊነቱ፣ ባለው የአሠራር ጥበብ፣ በተሠራበት ቁስ እና አስደናቂነት እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ባለው ሃይማኖታዊ ዕሴት በቋሚ ቅርስነት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡ የደብሩ ሙዚየም ባለመኖሩ ቅርሶቹ በዕቃ ቤት ውስጥ የተቀመጡ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
‎ቋሚ ቅርሱ የደረሰበትን ጉዳት መሠረት ተደርጎ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ጥገና እንደተደረገለት ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት ውስጣዊ እና ውጫዊ ጥገና የተደረገለት ሲኾን ማኅበረሰቡም ከሁለት ዓመት በላይ በነጻ በጉልበቱ አገልግሎት በመስጠት የበኩሉን አበርክቷል ብለዋል፡፡
‎በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ቅርሱን ከጸሐይ እና ከዝናብ ለመከላከል መጠለያ እንደተሠራለት ነው የገለጹት፡፡ ቅርሱን ከጉዳት ለመከላከል በወረዳው አሥተዳደር ምክር ቤት ከ500 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ ደረጃውን በጠበቀ የጎርፍ መቀልበሻ፣ ደጋፊ ግንብ እና የውኃ ስርገት መከላከያ ተሠርቶለታል ነው ያሉት፡፡
‎የሳርዝና ሚካኤል ትልቅ የቱሪዝም እምቅ አቅም ያለው እና በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የሚጎበኙት ቅርስ ነው ብለዋል፡፡ ከሌሎች በአካባቢው ከሚገኙ እንደ ላሊበላ እና ይምርኻነ ክርስቶስ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንዲሠራለት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
‎ዓመታዊ የንግሥ በዓሉ በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን የሚካኤል በዓል በድምቀት ይከበራል፤ በዕለቱም በርካታ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተለያዩ አካባቢዎች እንደሚታደሙበት ገልጸዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here