ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጉዛራ ቤተ መንግሥት የጎንደር የሥልጣኔ ዘመን ማሳያ ከኾኑት አብያተ መንግሥታት ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ቤተ መንግሥቱ በአጼ ሠርጸ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1556 ዓ.ም አካባቢ እንደተገነባም ይነገራል። የአካባቢውን መልክዓ ምድር ለመቃኘት እንዲያመች ተደርጎ የተሠራ ቤተ መንግሥት ነው። ከጣና ሐይቅ በቅርብ ርቀት ገደማ መገኙቱ ደግሞ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም እንዲኖረው አድርጎታል።
በወቅቱ የመጀመሪያው ባለ ሦስት ወለል ሕንጻ እንደኾነ የሚነገርለት የጉዛራ ቤተ መንግሥት በተለያዩ ዘመናት በደረሰበት ጉዳት የተለያዩ የጥገና ሥራዎች ተደርጎለታል።
ይሁን እንጅ ቅርሱ ሙሉ በሙሉ ጥገና ባለማግኘቱ አሁንም ድረስ ከጉዳት ሳይላቀቅ ቆይቷል። ቤተ መንግሥቱ በ2015 ዓ.ም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካኝነት የጥገና ሥራው ተጀምሮ እንደነበርም መዘገባችን ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ጥገናው በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት መቋረጡን የአካባቢው አስጎብኝ እና የሚመለከታቸው አካላት ገልጸውልናል። የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አስጎብኝ የኾነው ሳሙኤል መኮንን ከዚህ በፊት በወረዳው የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን በማስጎብኘት እና በማስተዋወቅ ይታወቃል።
በሰላሙ ጊዜ መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ በሚያገኘው ገቢ ራሱን እና ቤተሰቡን ከመምራት ባለፈ ከ80 ሺህ ብር በላይ ለወረዳው ገቢ ያደርግ እንደነበር ነው የገለጸው።
ይሁን እንጅ ከኮሮና ጀምሮ በተለይም ደግሞ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የቱሪስት ፍስሰቱ ቢያቆምም በወረዳው የሚገኘው የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና ሥራ የራሱን ድርሻ ሲወጣ እንደነበር ገልጾልናል።
ጥገናው ሲጠናቀቅ የተሻለ ዕድል ይዞ ይመጣል የሚል እምነት ቢኖረውም በሰላሙ ችግር የጥገና ሂደቱ ሊቋረጥ ችሏል። በጥገናው እና በተጓዳኝ ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበሩ ወጣቶች ከሥራ ውጭ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የተቋረጠው የቅርስ ጥገና እንዲቀጥል ከማኅበረሰቡም ጋር ውይይቶች ቢደረጉም አሁን ድረስ ሥራ አለመጀመሩን ገልጸዋል።
የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና ፕሮጀክት ኀላፊ በዛብህ መሠለ እንዳሉት የቤተ መንግሥቱ ጥገና በ2015 ዓ.ም ተጀምሮ በ2016 መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር ወደ ሥራ የተገባው ይላሉ።
ይሁን እንጅ የፕሮጀክቱ እስከ 60 በመቶ የሚኾነው ሥራ እንደተከናወነ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል ብለዋል።
በጥገና ሥራው ከ40 በላይ በአካባቢው የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የነበሩ ወጣቶች ተበትነዋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የቅርሱ የላይኛው ክፍል ወይንም ልባስ ጥገና ባለመደረጉ በዝናብ እና በፀሐይ ተጨማሪ ጉዳት እየደረሰበት እንደኾነም ገልጸዋል።
በቅርሱ ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የሚመለከታቸው ተቋማት ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ጥገናው እንዲቀጥል መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ማኅበረሰቡም ቅርሱ የራሱ ሀብት መኾኑን ተረድቶ የጥገና ሥራው እንዲቀጥል እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቤል መብት የቅርሱ የጥገና ሥራ በአብዛኛው ቢከናወንም በአካባቢው የጸጥታ ችግር ማጠናቀቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ሥራውን ለማስጀመር ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይቶች ተደርገዋል፤ ስምምነት ላይም መደረሱን ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶችም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አካባቢው ወደ አንጻራዊ ሰላም ከተመለሰ በቅርቡ ሥራው እንደሚጀምር ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!







