ብርኳኳ ማርያም

0
36

ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብርኳኳ ማርያም የአፄ ካሌብ የአምስተኛው ክፍለ ዘመን ሥራ የቡግና ታሪክ መሠረት እንደኾነች ይነገርላታል፡፡ ብርኳኳ ማርያም ቀድማ ታሪክን በመጀመር ለሌሎች መንገድ የጠረገች ነች፡፡ የሎዛ መንገድ ብለውም አባቶች ይጠሯታል፡፡

የኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ካሌብ ከአክሱም ታላላቅ ነገሥታት ቀጥሎ የነገሠ በኢትዮጵያ ገና እና ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበረው ታላቅ ንጉሥ ሲኾን ዘመነ መንግሥቱም ከ417 እስከ 527 ዓ.ም እንደነበረ የታሪክ ድርሣናት ያስረዳሉ፡፡

ብርኳኳ ማርያምም በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተች ይነገራል፡፡ ደብሯ በመጀመሪያ በድንኳን የተመሠረተች ስትኾን በኋላ በንጉሥ ካሌብ አማካኝነት በክብ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ተደብራለች፡፡

ብርኳኳ ማርያም አፄ ካሌብ በላስታ ከአቋቋማቸው አድባራት ከሳርዝና ሚካኤል፣ ዐርባዕቱ እንስሳ፣ ሸማይ ማርያም፣ ብልባላ ቂርቆስ እና ብልባላ ጊዮርጊስ አድባራት መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች፡፡

በብርኳኳ ማርያም የአፄ ካሌብ የንግሥና አልባሳት (ካባ፣ ለምድ እና ዘውድ)፣ ይቀመጥበት የነበረ ወንበር፣ የአሥተዳደር ማኅተሙ፣ ኩስኩስት እና የእጅ መታጠቢያ የመሳሰሉ ውድ ንዋያት በአሻራነት ይገኙባታል፡፡

የአካባቢው አባቶች የአፄ ካሌብ ሙሽራ ብለው የሚጠሯት ታሪካዊቷ የብርኳኳ ማርያም ሌላው አስደናቂ ታሪክ ከሰማይ የወረደ መስቀል በደብሯ የሚገኝ ሲኾን መስቀሉ ከቤተ ክርስቲያኑ በስተምሥራቅ በግ እየላሰችው ስለተገኘ በግ ጸድቃ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

አባቶች እንደሚሉት በአንድ ዘመን የአካባቢው ማኅበረሰብ በሀሰት መሃላ በመፈጸማቸው ሃምሳ ሰዎች በሰማይ ቁጣ እንደሞቱ ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ሃምሳ ፈጅ ተብሎም ይጠራል፡፡

ምንጭ፡- የሰሜን ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here