‎የደብረ ብርሃን ከተማ የኮሪደር ልማት ለቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ አለው።

0
53
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በአጼ ዘርያዕቆብ ዘመነ መንግሥት እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ጥንታዊቷ ከተማ ደብረ ብርሃን እድገቷን የሚያፋጥኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተሠሩላት ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ሳቢ እና ማራኪ በማድረግ የቱሪዝም ያለው አበርክቶ እየጓላ መጥቷል።
‎የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መሰረት ተክሌ በከተማዋ በኮሪደር ልማት ሰፊ የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገድ ተለይቶ መሠራቱ እና አረንጓዴ ልማቱ ጥሩ ገጽታ የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ በኮሪደር ልማቱ የተለየ ውበት መላበሷን እና ካላት ታሪክ ጋር ተዳምሮ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
‎ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አወቀ ደርሶ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ውብ እና ለነዋሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ ኹኔታ ፈጥሮላታል ነው ያሉት፡፡ በልማት ሥራው የተሠሩ የእግረኛ መንገዶች ከተሸከርካሪ ጋር በመጋፋት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡ ከተማዋን አረንጓዴ የማድረግ ሂደት ለጉብኝት ተመራጭ እንድትኾን የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
‎የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አክሊል ጌታቸው የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ በማሻሻል ለቱሪስቶች ምቹ ኹኔታ የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ቱሪስቶች ከሆቴል ወጥተው በከተማው በመንቀሳቀስ ስለአካባቢው ለማወቅ እና ለመዝናናት የሚያስችል ኹኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
‎የከተማዋ ንጹሕ እና አረንጓዴ መኾን ለነዋሪዎች እና ለቱሪስቶች ጤናማ የሚያደርግ እና ደስታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል። መንገድ ላይ የነበሩ ለእይታ ብክለት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ምሰሶዎችን ያስወገደ እና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
‎ከተማዋ እንደ ቱሪስት መዳረሻነቷ የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ መስህብ ነው፡፡ ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሆቴሎች እንዲገነቡ፣ ለቱሪስት ፍሰት መጨመር እና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
‎የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የመሠረተ ልማት መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ነብዩ ባዩ በከተማው የ15 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለመሥራት ዲዛይን መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ተሠርቶ ተጠናቋል፤ በዚህ ዓመትም ሦስት ኪሎ ሜትር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎የነዋሪዎችን የእንቅስቃሴ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ማለትም በእግር፣ በብስክሌት እና በሌሎች ተሸከርካሪዎች ለመንቀሳቀስ መንገዶች ምቹ ኾነው ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡
‎ሕንጻዎች እና ትንንሽ ግንባታዎች በስታንዳርድ የከተማው ቀለም እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ይህም ከተማዋን ለነዋሪዎች እና ለቱሪስቶች ምቹ እና ያማረ ገጽታ እንዲኖር አስችሏታል ነው ያሉት፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here