“ጥርን በባሕር ዳር አይቀርም” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

0
74

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ ‘ጥርን በባሕር ዳር’ መርሐ ግብር አንዱ አካል የኾነው ከተማ አቀፍ የባሕል እና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የጥር ወር እንደ ከተማም ይሁን እንደ ክልል በርካታ ሁነቶች የሚከናወኑበት ነው ብለዋል።

የቀደሙት ትውልዶች ያቆዩትን ባሕል በመጤ ባሕል ሳይበረዝ ቀጣዩ ትውልድ እንዲያስቀጥለው ማድረግ የሥራቸው አካል አድርገው እየሠሩ መኾኑን አስገንዝበዋል።

የባሕል ፌስቲቫሉ የማኅበረሰቡ ቱባ ባሕል ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግን ዓላማ ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል መካሄዱ ከተማዋን በአስተማማኝ የሰላም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

“ጥርን በባሕር ዳር አይቀርም” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥርን በባሕር ዳር በድምቀት ለማክበር በርካታ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሕር ዳር መጥተው እንዲጎበኙ እና በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው የባሕል ፌስቲቫሉ የባሕል እሴቶችን ለማስተዋወቅ፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማጎልበት እና ነባር እሴቶችን ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ መኾኑን አንስተዋል።

በመርሐ ግብሩ በከተማዋ ያሉ የባሕል፣ የኪነ ጥበብ እና እደ ጥበብ ውጤቶች መቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

በፌስቲቫሉ የባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ እያቀረቡ አሚኮ ያገኛቸው ወይዘሮ እንይ ጋሹ መርሐ ግብሩ የቆዩ ባሕላዊ እሴቶች የቀረቡበት እና ደስ የሚል ነው ብለዋል።

ባሕላዊ እሴቶች ሳይበረዙ በማቆየት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲህ አይነት መርሐ ግብሮች ጥሩ አጋጣሚ እንደኾኑ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here