ቤዛ ኩሉ ዓለምን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው።

0
64
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት መካካል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዱ ነው።
የሃይማኖቱ ተከታዮች 44 የጾም እና የጸሎት ቀናትን አሳልፈው የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰው እና መላእክት አንድ ኾነው ያመሰገኑበት፣ ሰማይ እና ምድር አንድ የኾኑበት እንደኾነ የተናገሩት በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ትርጓሜ መጻሕፍት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ ናቸው።
በዓሉ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ቢከበርም በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ደግሞ ከሌላው አካባቢ በተለየ ሁኔታ በቤዛ ኩሉ ዓለም ሥርዓት ደምቆ ይከናወናል።
ቤዛ ኩሉ ዓለም የዓለም ሁሉ መድኃኒት ማለት ሲኾን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ለዓለም ሁሉ ቤዛ የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ዕለት የሚታሰብበት እንደኾነ ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል ገልጸውልናል።
የበዓሉ አከባበር ጠዋት ከላይ “ማሜ ጋራ” እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ አናት ላይ፣ ከታች ደግሞ በቤተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ ካህናቱ ከላይ እና ከታች ኾነው ዝማሬ ያቀርባሉ።
ከላይ ያሉት ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም መወለድን አስመልክቶ መላእክት ከሰማይ ኾነው ያመሰገኑበትን ምሳሌ ያመለክታል። ከታች ያሉት ካህናት ደግሞ እረኞች ከምድር ኾነው ያመሰግኑ የነበረውን ምሳሌ የሚያሳይ እንደኾነ ነግረውናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል አከባበር ከዋዜማው ጀምሮ የምሽቱ ማሕሌት ተቁሞ የሌሊቱ ቅዳሴ እንዳበቃ የበዓሉ ፍጻሜ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በላሊበላ ግን የሌሊቱ ቅዳሴ ካበቃም በኋላ እስከ ረፋድ ድረስ ካህናት በጃኖ የታጀበ የባሕል አልባሳት፣ ልብሰ ተክህኖ፣ ካባ ደርበው በተለየ ድምቀት በዓሉን እንደሚያከብሩት ነው የተናገሩት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ደምቆ እንዲከበር እና እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻነት ኾኖ እንዲያገለግል መሥራት ይገባል ብለዋል። ይህንን የተለየ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥናት እየተደረገ መኾኑን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ገልጸዋል።
ይህም ተግባራዊ ሲደረግ ለአካባቢው የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ መነቃቃትን ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here