ቅርሶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑን የላሊበላ ባሕል ማዕከል ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

0
49

ባሕር ዳር፡ ጠር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ላስታ፣ ላሊበላ እና አካባቢው የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች መገኛ ነው።

አካባቢው ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን እና ለምክክር የተቀመጡ አዛውንቶች የሚመስሉ ውብ ኮረብታዎችን የያዘ መልክዓ ምድር ባለቤትም ነው።

ከሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ባለፈ በተለያዩ ባሕላዊ እሴቶች የበለጸገ አካባቢም ነው። እነዚህን የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች እንዲሁም የማኅበረሰቡን ባሕል እና ወግ ሰንዶ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የባሕል ማዕከል እየተገነባ መኾኑን የላሊበላ ባሕል ማዕከል ጽሕፈት ቤት አደራጅ ባለሙያ ደሳለኝ ማሞ ገልጸዋል።

ባለሙያው እንዳሉት የባሕል ማዕከሉ በ2000 ዓ.ም በ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ብር የማቋቋም ሥራ ተሠርቷል። ከተቋቋመ ጀምሮ በላሊበላ እና አካባቢው በሀገር በቀል ዕውቀት የተሠሩ ባሕላዊ ቅርሶችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ የምስል እና የፎቶ ሙዚዬም፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የጥናት እና ምርምር ማዕከል፣ የኮምፒውተር ማዕከል፣ ሬስቶራንት እና የእንግዳ መቀበያዎችን ማደራጀት ተችሏል ብለዋል።

የባሕል ማዕከሉ መደራጀት የአካባቢውን ታሪክ፣ ባሕል እና ወግ ለመጠበቅ እንዲሁም ጥናት እና ምርምር ለማካሄድ ያግዛል። ለአካባቢውን ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ገቢን ለማሳደግም ያስችላል ነው ያሉት።

የባሕል ማዕከሉ በ3 ሺህ ስኩዬር ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here